እዋናዊ ቃለ-መሕትት ምስ ኣቦ መንበር ህ.ወ.ሓ.ት ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል

ሼር/ላይክ

ተኸታተልቲ

4925704
Today
Yesterday
This Week
Last Week
This Month
Last Month
All days
3109
2784
12607
4892207
68286
89679
4925704

Your IP: 54.224.94.8
2018-03-21 20:46

"ተወዳድረህ ለማሸነፍ የራስ ጥረት ስለሚጠይቅ አመራሩ የራሱን ድክመት ለመሸፈን ህወሓት ላይ፣ የትግራይ ህዝብ ላይ መንጠልጠል ይፈልጋል፡፡"

here we go
selam new

 

ጓድ ከበደ ጫኔ፣ የፌደራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደሮች ሚኒስቴር ሚኒስትር

በኣባዲ ገ/ስላሴ                              

ኢህአዴግ መንግስት ሆኖ እችን አገር በመራባቸው ዓመታት በአገሪቱ ተአምራዊ የሚባል ለውጥ ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ይህንን የሆነው  የዚች አገር የቆየ ውስጣዊ ችግር በመረዳት መፍትሔ ማስቀመጥ የሚችል ድርጅት በመገኘቱ ምክንያት ነው፡፡ ኢህአዴግ የህዝቦችን እኩልነት ለማረጋገጥ፣ በዚች አገር ለዘመናት ለተንሰራፋው ድህነትና ሁላቀርነት ለማጥፋት እንዲሁም ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ትኩረት ሰጥቶ በሰራቸው ስራዎች አገሪቱ ከቁልቁለት ጉዞ ተመልሳ አንገትዋን ቀና ማድረግ ጀምራለች፡፡ ከልመና፣ ተመፅዋችነትና አገራዊ ውርደት ወጥታ የተስፋ ምድር መሆን ችላለች፡፡ የአገራችን ድል በዚሁም ሳያበቃ የአፍሪካ  ቀንድ የሰላም ጠባቂና የአህጉራችን አፈ ጉባኤ መሆን ችላለች፡፡ ይህ በሆነበት ጊዜ አገራችን ውስጥ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ከምንም በላይ ግን ህግና ስርዓት በተተከለበት ሃገር የሰው ህይወት በከንቱ የሚጠፋበት፣ የሰው ንብረትና ሀብት የሚወድምበት፣ ወንድምና የአንድ አገር ህዝብ በጥርጣሬ የሚተያይበት ምልክት የገባንበትና በአጠቃላይ በስንት መስዋእትነት የተረጋገጠ ሰላም ደፍርሶ አገሪትዋን መስቀለኛ መንገድ ላይ የቆመችበት ሁኔታ ተከቷል፡፡

ኢህአዴግ "የችግሩንም የመፍትሄውም ቁልፍ እኔ ጋር ነው" በማለት ችግሮቹን ከነስርመሰረታቸው ለመፍታት ጥልቅ የተሃድሶ መድረክ እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ያደረገው የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ መድረክ ምን ይዘቶች እንደነበሩትና ወዴት ሊወስደን እንደሚችል፣ ከኢህአዴግ ስራ አሰፈፃሚ መድረክ ቀጥሎ ግምገማ እያደረገ ስላለው ብአዴን፣ ስለ ህወሓትና ብአዴን፣ ሰለትግራይና የአማራ ህዝብ፣ በአማራ ክልል በትግራይ ህዝብ ላይ አነጣጥረው እየደረሱ ስላሉ አጠቃላይ ጥቃቶችና ሌሎችም ክስተቶች መሰረት በማድረግ የፌደራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደሮች ሚኒስትር ሚኒስትሪ ጓድ ከበደ ጫኔን በእንግዳነት በመጋበዝ ለጠየቅናቸው ጥያቄዎች ያቀረብሉንን ዝርዝር ሀሳቦች አቅርበናል፡፡

ወይን፣ ቃለ መጠይቁ ኢህአዴግ የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማውን ካጠናቀቀ በኋላ ነው እያካሄድነው ያለነውና ለመሆኑ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ወደ እንደዚሁ አይነት የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ መድረክ ለምን ገባ?

ጓድ ከበደ፣ ኢህአዴግ ወደ ተሃድሶ መድረክ የገባው በውስጡ ያጋጠሙ ችግሮች በመኖራቸው ምክንያት ነው፡፡ የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው የተጀመረው 2008 ዓ/ም መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ግምገማው ያኔ ሲደረግ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው የነበሩት፡፡ አንደኛው ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታት የተካሄዱት የተሃድሶ እንቅስቓሴዎች በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ የሚለውን ነገር በዝርዝር መገምገም ኣስፈላጊ ስለነበረ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ወቅታዊ ችግሮች  እየተባባሱ  እዚህም እዛም ግጭቶች እየተከሰቱ ግን ደግሞ "ይጠፋሉ" ሲባል እንደገና ብልጭ ድርግም እያሉ የቀጠሉበት ሁኔታ ስለነበረ የህዝቡ የልማትና የመልካም ኣስተዳደር ጥያቄዎችም እየገፉ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ በኣጠቃላይ የአስራ ኣምስት አመት ጉዞ ግምገማ እቅድ ኣቅዶ ነበር የጀመረው፡፡ይህን ሲደረግከ2006 ዓ/ም ጀምሮ በአንድንድ የኦሮሚያና አማራ አከካባቢዎች እየተከሰቱ የመጡት ችግሮች የበለጠ ተሃድሶው እንድናካሂድ ግፊት ያደረገ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ግን ድርጅታችን ኢህአዴግ አገሪቱ በምትገኝበት አጠቃላይ ሁኔታዎችና ችግሮች  መሰረት  በማረግ  የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ኣካሂደዋል፡፡ ይህን ግምገማ ከአንድ ዓመት በኋላ ሲገመገም የቀረፋቸው ችግሮች አሉ፡፡ግን ደግሞ ችግሮቻችንን ስርነቀል በሆነ መንገድ ኣልተፈቱም፡፡ ባለመፈታቸው ምክንያት እንደገና ችግሩ ኣገርሽቶ ዳግም ወደ ተሃድሶ ገብተን እንደገና እንድንገመግም ኣስገድዶናል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ የአሁኑ የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ማካሔድ ያስፈለገበት ምክንያት ኢህኣዴግ በመጀመርያው የጥልቅ ተሃድሶ መድረኩ የራሱ ውስጣዊ ችግሮች ፈትቶ የህዝቡ የልማት፣ የመልካም ኣስተዳደር ጥያቄዎች ይፈታል የሚል ተስፋ ተይዞ በነበረበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መለወጥና መታደስ ባለመቻላችን ምክንያት እንደገና ችግሮቹ ኣገርሽተው ከዚሁ በተጨማሪም በቢሄራዊ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከልም መጠራጠርና ኣለመተማመን እየነገሰ መጥቶ መጨረሻ ላይ ለግጭቶች መስፋፋትም ችግሮቹ ላለመፈታትም መሰረታዊ ጉዳይ ሆኖ ነው ስለተገኘ ነው፡፡ ይሄ በመሆኑ ምክንያት እንግዲህ የኢህኣዴግ ስራ ኣስፈፃሚ እንደገና ቁጭ ብሎ እንዲገመግም ኣስገድዶታል ማለት ነው፡፡ ይሄ ነው መነሻው፡፡

ወይን፡-ኢህአዴግ እንደ ድርጅት የጥልቅ ተሀድሶው መድረክ የጀመረው ክረምት 2008 ዓ/ም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ያኔም ችግሮቹ ለይቶ የመፍትሄ አቅጣጫወቹም እንዳስቀመጠ የሚታወስ ነውና የአሁኑ መድረክ ካለፈው የተሀድሶ መድረክ በምን ይለያል?

ጓድ ከበደ፣  ያሁኑ የተሃድሶ መድረክ  ከባለፈው የተሃድሶ መድረክ የሚለየው የባለፈው ተሃድሶ በመሰረቱ ለአባል ድርጅቶቹ የተተወ ተሃድሶ ነው የነበረው፡፡ ኣባል ድርጅቶቹ በራሳቸው ብሄራዊ አኗኗር፣ በራሳቸው ድርጅታዊ አጥር ውስጥ ግምገማ ኣድርገው፣ ሂስና ግለ ሂስ ኣካሒደው 'በኣመራር መቀጠል ያለበትም የሌለበትም' ራሳቸው አጥርተው በራሳቸው ርቀት እንዲሄዱ የተተወ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በኢህኣዴግ ደረጃ በተቀመጡ ወሳኝ በሚባሉት ጉዳዮች  መግባባት ላይ ተደርሶ፤ ያን መሰረት በማድረግ እያንዳንዱን ድርጅት ከራሱ ሁኔታ ኣጣጥሞ ግምገማው እንድያስቀጥል ተደርጎ ነበር፡፡ ይሄ በመሆኑ በኢህአዴግ ደረጃ የነበሩት ችግሮች በስር ነቀልነት በሚገባ ሳይፈቱ ሰውም ሃሳቡ በነፃነት ገልፆ ውይይት ሳያደርግበት፣ በሚገባ ሳይተማመንበት የተካሄደ ተሃድሶ ስለነበረ እንደ ኢህኣዴግ ሲገመገም መሰረታዊ ለውጥ የመጣበት ሆኖ ኣልተገኘም፡፡ለምሳሌ ያኔ ህወሓት በተሻለ ርቀት ከቢሄራዊ ድርጅቶቹ  ሂደዋል ብለን ነበር የገመገምነው፡፡ የብአዴንም ቢሆን ወጣ ገባነት ቢኖሮውም የተሻለ ርቀት ለመሄድ ሞክረዋል ብለን ገምግመን ነበረ፡፡ ሌሎች ድርጅቶችም ከነበሩበት ተንፏቀውም ቢሆን ጥሩ ተጉዘዋል ብለን ነበር የገመገምነው፡፡ ግን ኣሁን ሆነን ስናየው ችግሮቹ ተባብሰው፣ ተቀጣጥለው ስናያቸው ምን ያክል ውስጣችንን  በእውነት ያላየን እንደነበርን  እንደ ኢህኣዴግ ተመለክተናል፡፡

ስለዚህ እንደ ኢህኣዴግ ስራ ኣስፈፃሚ አሁን ግምገማው ሲያደረግ ድርጅታዊ አጥር ሳይከልል ከሰማይ በታች ያለ በሙሉ በየተኛውም ግለሰብ በየተኛውም ድርጅት ላይ የፈለግነው ነገር እንድናነሳ ዕድል የሰጠ ነበረ፤ ያሁኑ የስራ ኣስፈፃሚ መድረክ፡፡ የአሁኑ መድረክ ስንጀምር "ከራሳችንም በላይ የሃገር ህልውና እናድን" በሚል ኣቅጣጫ  ነው የገባነው፡፡ የድርጅታችን ህልውና እናድን፡፡ የህዝባችንን አንገብጋቢ ችግሮች እንፍታ፡፡ ለራሳችን ክብር ለራሳችን ቦታ መስጠት እናስወግድ፡፡ ከኛ በላይ ኣገር መቅደም አለበት፡፡ ከኛ በላይ ድርጅት መቅደም አለበት፡፡ ከኛ በላይ ህዝብ መቅደም ኣለበት፤ የሚል መተማመን ይዘን ነው ወደ መድረኩ የገባው፡፡ ከዚህ ኣቐጣጫ ኣንፃር "ከዚህ ዓመት ወይም ከዚህ ሁለት ዓመት ጀምረው የነበሩትንን ችግሮች ምናምን ብለን ሳይሆን "የዛሬ ኣስራ ኣምስት ዓመትም ከዛ በፊትም ይሁን  የሚነሳ ነገር ወይም ችግር ካለ ምንም ዓይነት ገደብ ሳይደረግበት እንደፈለገ እንድያነሳ፣ በግለሰብ የሚያነሳው ነገር ካለ፣ በቡድንም የሚያነሳው ነገር ካለ፣ በድርጅትም የሚያነሳው ነገር ካለ ምንም ዓይነት የሚገደብ ነገር ሳይኖር በነፃነት እንድንገማገም ነው የተደረገው፡፡

ይሄን ማድረግ በመቻላችን በጣም በርካታ ያልተፈቱ ቅሬታዎች እንደነበሩብን ማየት ችለናል፡፡ ስለዚህ ከላይ የተግባባን እየመሰለን ሳንግባባ የወጣንባቸው መድረኾች እንደነበሩ ነው የተመለከትነው፤ በዚህ የአስራ ሰባት ቀን ግምገማ፡፡ በግምገማው ምንድን ነው የታየው? በተለይ መጠራጠሩ እና አለመተማመኑ በጣም ጫፍ የነካ ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡ ብአዴን ህወሓትን ይጠረጥራል፣  ኦህዴድ ብአዴንን ወይም ህወሓትን ይጠረጥራል፤ ህወሓት እንደገና ብአዴንን ወይም ኦህዴንን ይጠረጥራል፡፡ እርስ በራሳቸው እየተጠራጠሩ የሐሳብና የተግባር አንድነት ሳይኖራቸው "ድርጅታዊ" የሚባሉ ተልዕኮዎች በዴሞክራሲያዊ ማእከልነት ለመተግበር እያቃታቸው ሁሉም በየራሱ መንገድ የሚሄድበት ሁኔታዎች ሰፍተው የተገኙበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ የውስጥ ድርጅታዊ ዴሞክራስያችን የተበላሸ ገፅታ እንደነበረው ነው የተመለከትነው፡፡ ሰዎች በብዱንም ይሁን በግለ ሰው ደረጃ የመሰላቸውን ተናግረው ተከራክረው ያመኑበትን እንዲተገብሩ በማድረግ ረገድ ውስጠ ድረጅት ዴሞክራስያችን እየጠበበ መምጣቱ ድሮ ኢህኣዴግ የነበረውን ባህርይ እየሳትን ወደ አልሆኑ ፅንፍ የሄድንባቸው ሁኔታዎች እንደነበሩ በጥልቀት ነው  የተገመገመው፡፡ በመሆኑም የውስጠ ድርጅት ዲሞክራሲያዊ ሁኔታችንን በመገምገም ነበረ ሰፊ ጊዜ ወስደን የተነጋገርንበት፡፡

ይህንን ስናይ አንደኛ፣ በራሳችን ነፃነት የለንም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በውስጣችን ኣደርባይነት ነግሰዋል፣ ፀረ ዲሞክራሲ ነገሰዋል፣ መርህ ኣልባ ግንኙነት እየጠነከረ መጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰዎች ሀሳባቸው እንደልባቸው የሚያንሸራሽሩበት ሳይሆን እየተገደቡ የሚሄዱበት ገፅታ እንዳለ በዝርዝር የገመገምንበት መድረክ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትምዴሞክራሲ ሲባል የውስጠ ድርጅት ዴሞክራስያችን ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች፣ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን፣ የእንባ ጠባቂ ተቋሞች፣ ሚድያዎች ፣ የብዙሐንና ሞያ ማሕበራት፣ ወዘተ በሙሉ ነፃነታቸው ጠብቀው እንዲታገሉ በማድረግ ድርጅት በደከመበት ግዜ መንግስቱን ሂስ የማድረግ፣ እንዲስተካከል የማድረግ፣ ጠንካራ ቁመና እንዲኖራቸው ኣድርጎ በመቅረፅ ረገድ ትክክለኛ ኣካሄድ ያልሄድን መሆናችን ያለፈው ጉዟችን ስንገመግም ተመልክተናል ኣይተናል፡፡ ስለዚህ ምንድነው? እያንዳንዱ ብዙሐን ማሕበራት በራሳቸው ነፃነት ቆመው እንዲታገሉ ማድረግ፣ ማህበራቱ በነፃነት የራሳቸውን መሪዎች እንዲመርጡ፣ የዴሞክራሲተቋማት የራሳቸው የቤት ስራ እንዲሰሩ፣ ፓርቲዎች ብቁ ተዋደደሪዎች እንዲሆኑ አድርጎ መቅረፅ ላይ ከዴሞክራሲ አንፃር የጎደሉ ጉድለቶችና ውሱንነቶች እንዳሉ ለማየት የቻልንባቸው ሁኔታዎች ናቸው የነበሩት፡፡

 ከዚህ በመነሳት ላለፉት 27 ዓመታት ለምንድነው ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በህጋዊ መንገድ የሚታገሉ ፓርቲዎች መፍጠር ያልቻልነው? ለምንድነው ላለፉት 27 አመታት ጠንካራና በነፃነት የሚንቀሳቀሱ ሚድያዎች መፍጠር ያልቻልነው? ለምንድ ነው አሁን ያሉት የመንግስትም ሆኑ የየክልሉ ሚዲያዎች እርስ በርሳቸው የሚጎነታተሉ?፣ እርስበርሳቸው ግጭትን የሚያስፋፉ?፣ ዘረኝነትን  የሚሰብኩ? የግንባታ ስርአታችን በራሱ ችግር የነበረበት ነው ብለናል፡፡ በልማታዊ ኣስተሳሰብ ቅኝት፣ በዲሞክራሲያዊ ኣስተሳሰብ ቅኝት ተቃኝተው ሚዲያዎች የህዝብ  መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ስራ ባለመስራታችን ምክንያት የተፈጠረ ችግር ነው ብለን ገምግመናል፡፡

 የኦሮምያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ግጭት ሲነሳ የሁለቱ ክልል ሚድያዎች ምንም የዲሞክራሲ ሽታ ኣልነበራቸውም፡፡ አንዱ በሌላው ላይ የማጥቃት ዘመቻ ነው ሲያካሂዱ የነበረው፡፡ በአማራና በትግራይ መሃከል ግጭቶች ሲከሰቱ ወይም ደግሞ የትግራይ ተወላጆች ከጎንደርም ከሌሎች አካባቢዎችም መውጣት ሲጀምሩ የአማራ ክልል ሚዲያ ሲሰራው የነበረው የማቀጣጠል ስራ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሚድያዎች ፌደራል ስርአቱን ተንከባክበው፣ ፌደራል ስርኣቱን ጠብቀው ከመታገል ይልቅ የፌደራል ተቋማት የማፍረስና የመጠራጠር ባህሪ ነው  የነበራቻው፡፡ መከላከያ እየጎዳን ነው፤ መከላከያ ጥቃት እየሰነዘረብን ነው፤ የፌደራል የፀጥታ ሃይሎች የኛ ተቋማት ኣይደሉም፣ ይውጡልን፤ የሚል ኣመለካከት ከጠላት አመለካከት ጋር አንድና ያው ሆኖ የተገኘበት ገፅታ ነው የነበረው፡፡ ስለዚህ ይህ ሁሉ ስናየው የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታችን ችግር እንደነበረበት ነው የተገመገመውና የታየው፡፡

ወይን፣ በመጀመርያው የጥልቅ ተሀድሰው መድረክ፣ ኢህአዴግ ችግሮችን በሚገባ ለይቶ ስያበቃ "ችግሮቹ ባለቤት ስላልነበራቸው ችግሮቹን መፍታት አልተቻለም" የሚል አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ነበሩ፡፡ በርግጥም ችግሮቹ ሳይፈቱ ዘልቀው ወደ ባሰ ሁኔታም ገብተናልና የአሁኑ የኢህአዴግ የግምገማ ስልት ይህን ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር ማለት እንችላለን ወይ? አሁንም ቢሆን በተለይ ከብሄራዊ ድርጅቶች ኣካባቢ "ግምገማው ከሰው ጋር ላይገናኝ ይችላል" የሚል ስጋት አለ፤ እዚህ ጋ ምን ማለት እንችላለን?

ጓድ ከበደ፣ እንግዲህ በዚሁ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ግምገማ የተመለከትናቸው ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛ ባለፉት 27 ኣመታት ባካሄድነው ትግል በሃገራችን የተመዘገቡ ለውጦች እጅግ የሚያስጎመጁ ናቸው ነው፡፡ በጣም ጥሩ የልማት ውጤቶች አስመዝግበናል የሚል ግምገማ ኣካሂደናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለልማት እድገቱ ሊመጥን የሚችል ስትራተጂካዊ ኣመራር ኣልሰጠንም ብለናል፡፡ ልማቱን ሊመጥን የሚችል ስትራተጅካዊ ኣመራር ባለመስጠታችን ምክንያት እዚህም እዚያም ችግሮች እየተከሰቱ ናቸው፡፡ የአመራር አቅማችን ተዳክመዋል፡፡ "ይህንን መለወጥ መቻል አለብን" ነው ያልነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ሲታሰብ በጥልቅ ተሃድሶአችን የታዩ ጉድለቶች አሉ፡፡ ቅድም እንዳልኩት ስትራተጂካዊ ኣመራር የሚሰጡት ሰዎች ላይ የአቅም መዳከም ተከስቷል፡፡ መሰረታዊ ፖለቲካዊ አመራር ከመስጠት ይልቅ በጊዝያዊ ችግሮች ላይ የመታጠር፣ በጊያዊ ችግሮች ላይ የመወጠር ሁኔታዎች ተከስተዋል፡፡ ስለዚህ ችግሮቹ ስር ነቀል በሆነ መንገድ የማይገመገሙበት፣ ችግር መስማት  የተሳነው ኣመራር እየሆነ የመጣ መሆኑ የታየበት፣ በስልጣን ሽኩቻና በአደርባይነት እርስ በራሱ እየተገፋፋ የመጣ ኣመራር መሆኑ የታየበት፣ በዚህም ፀረ ዴሞክራሲ እየነገሰ የመጣበት፣ "ኣዲስ ነገር የለም ሁሉም ነገር ተመልሰዋል" የሚል አስተሳሰብ እየነገሰ ግን ደግሞ በመርህ አልባ ግንኙነት ሰዎች በኔትዎርክ እየተሳሰሩ አንዱ ሌላውን የሚያሸማቅቅበት፣ በአጠቃላይ የሃሳብና የተግባር አንድነት በድርጅት ውስጥ የተዳከመበት ሁኔታ ነው ተፈጥሮ የታየው፡፡ ይሄ ብቻ ሳይሆን በነባሩና  በአዲሱ ኣመራር መካከል እንደዚሁ መሳሳብ የነበረበት ነው፡፡ ነባሩ ኣመራር "ኣዲሶቹ ናቸው በብቃት መምራት ያልቻሉ" ይላል፡፡ አዲሱ ኣመራር ደግሞ "ነባሮቹ እኛን ማገዝ መደገፍ ሲገባቸው እኛን በአሉታ ብቻ ይገመግሙናል" የሚል አስተሳሰብ ይዘው የቆዩበት ሁኔታዎች ነበሩ፡ እነዚህ ተደማምሯቸው  ችግሮቹ እየገዘፉ መጥተዋል፡፡አሁን ይሄን ችግር በመገምገም መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት አለብን የሚል መተማመን ላይ ነው በግምገማው የተደረሰው፡፡

እዚሁ መተማመን ላይ ስንደርስ ኢህኣዴግ እያንዳንዱ አባል ድርጅት ላይ ገብቶ እከሌ ይውረድ "እከሌ ይቀጥል" ወይም "እከሌ እንደዚህ ይሁን" ማለት ኣይችልም፡፡ ህገ መንግስቱም የድርጅቱ ስርዓትም ኣይፈቅድለትም፡፡ ኢህአዴግ የሁሉም ኣባል ድርጅቶች ግምባር ስለሆነ ለግንባሩ የተሰጡት ስልጣንና ሃላፊነቶች ድርጅታዊ ነፃነታቸውን ጠብቀው በራሳቸው እንዲገመግሙ የሚያድረግ ነው፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ  የኢህኣዴግን ዴሞክራሲያዊ ኣሰራር ተከትሎ ድርጅቶቹ በነፃነት የራሳቸውን ኣመራር ገምግመው ብቁ የሆነውን ወደ ሃላፊነት የማውጣት፣ ብቁ ያልሆነውን ደግሞ ከሃላፊነቱ ዝቅ የማድረግ ሃላፊነት የሚወስዱት አባል ድርጅቶቹ ናቸው የሚሆኑት፡፡ ስለዚህ ኢህኣዴግ እንደስራ አስፈፃሚ ይሄን የማድረግ ስልጣንና ሃላፊነት የለውም ማለት ነው፡፡ ታድያ ምንድነው የተደረገው? ከተባለ፣ አንደኛ በአጠቃላይ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ኣመለካከትና የፀረ ህዝብ ኣመለካከት የተቀላቀሉበት የጎራ መደባላለቅ የታየበት ሁኔታ ነው ያለው ብለን ነው የገመገምነው፡፡ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት  "እያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት በዚህ መድረክ ራሱን ማጥራት መቻል ኣለበት" ብለናል፡፡  በውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ላይ፣ በሙስናና በብልሹ ኣሰራር ላይ፣ በዴሞክራሲያዊ ስርኣት ግንባታ ላይ፣  በአጠቃላይ የድርጅት ግንባታ ጉዳዮች ላይ፣  በፌደራል ስርአቱ ኣተረጓጎምና የጋራ ህልውናችን ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን እያንዳንዱ ኣባል ድርጅት አመራሩን ሂስና ግለ ሂስ ኣድርገው በሚገባ ገምግመው ተጠያቂ የሚሆኑ ኣመራሮችን ተጠያቂ ማድረግ መቻል ኣለበት" የሚል የጋራ ኣቋም ነው የተያዘው፡፡

ይህን ሲደረግ ኢህኣዴግ  ያዘጋጀው ሰነድ አለ፡፡ እያንዳንዱ ድርጅት ደግሞ በዛ ሰነድ መነሻ ኣድርጎ የራሱ የመገማገምያ ሰነድ ኣዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ በመነሳት እያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት ራሱን ይገመግማል፡፡ ሁሉንም ቁጭ ብለው ከራሳቸው ሁኔታ አዛምደው ይገመግማሉ፡፡ ለምሳሌ እንውሰድና ብአዴን ለምንድነው በአማራ ክልል የትግራይ ህዝብና የአማራ ህዝብ በአንድነት ታግሎ እያለ፣ በአንድ ምሽግ ወድቆ እያለ፣ በጋራ እየታገሉ መጥተው እያለ ዛሬ በዘረኝነት የትግራይ ተወላጅ የሆነ ቤት የሚያቃጥልበት፣ ለምንድነው የትግራይ ተወላጅ የሆነውን "ውጣ" እየተባለ የሚያባርርበት?  ዘረኛ የሆነ አስተሳሰብ እሚነግስበት ምክንያት ምንድነው? ከዚህ ረገድ ከላይ ከአናቱ ጀምሮ እስከታች ድርስ  በየደረጃው ያለው የአመራር አካል በደንብ መፈተሽ መቻል ኣለበት፡፡ የተደበላለቀ ኣመለካከት ይዞ፣ የጠላትን ኣቋም ይዞ እሚንቀሳቀስ ሃይል ካለ በውስጡ ማጥራት ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት የሚቆሙ ሃይሎችን በውስጡ እየታገለ "ዴሞክራቲክ" ያልሆኑ ሃይሎችን ደግሞ ሂስ እያደረገ እንዲስተካከሉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ካላስተካከሉ ደግሞ መስመራቸውና ኣስላለፋቸው እንዲለዩ ማድረግ ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡

 ይሄን ለማድረግ ድርጅቱ ተልእኮ ወስዶ ግምገማ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሌሎችም ለምሳሌ ኦህዴድም በተመሳሳይ መንገድ የኦሮሞ አንድነትን ለማምጣት የሁሉም ኦሮሞ አንድነትን ኣይደለም የሚፈለገው፡፡ ተመሳሳይ እምነትና ኣቋም ያላቸው መደባዊ ኣሰላለፋቸው፣ ማህበራዊ መሰረታችን የሆኑ ሃይሎችን ኣሰልፎ ግን ደግሞ የኦነግን የጠባብ ኣስተሳሰብ ያላቸው ሃይሎች ለይቶ የሚታገልበትን ሁኔታ መፍጥር መቻል አለበት፡፡ ኣለበለዚያ በስመ ኦሮሞ አንድነት በዘር፣ በደም የተሳሰረ ሁሉም አንድ ላይ የሚሆን ከሆነ ምንም አይነት መደባዊ ኣሰላለፍ የለውም ማለት ነው፡፡ ማህበራዊ መሰረቱን የለየ የትግል ኣቅጣጫ የለውም ማለት ነው፡፡ ይሄ ከሆነ ደግሞ አደጋ ኣለዉ፡፡ ስለዚህ ኦህዴድም ቁጭ ብሎ ራሱን ለምንድነው ከሌላው ሃይል ጋር በአንድነት የተቀላቀለ ነው? ለምንድነው ከነዚህ ሀይሎች ጋር ኣብረን የተሰለፍነው? ለምንድነው ማህበራዊ መሰረታችንን ማእከል ያደረገ የትግል ኣቅጣጫ ያልተከተልነው? ብሎ ራሱን በውስጡ መገምገም ኣለበት፡፡

 በዚህ ረገድ ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር የተያያዙ፣ ከሙስና ጋር የተያያዙ፣ ጎዶችን ጉዳጉድን በደንብ ራሱን መፈተሽ ኣለበት፡፡ ከጠባብነት አስተሳሰብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በደንብ መፈተሽ አለበት፡፡ ከሌላው ህዝብ ጋር በአንድነት እንዳይኖር የሚያደርጉት እንቅፋቶች ምን እንደሆኑ ነቅሶ አውጥቶ የማያዳግም ትግል ማድረግ ይጠብቅበታል፡፡ እንደዛ ስናደረግ፣ ማለትም ሁላችን በየድርጅታችን የድህረት ኣመለካከት የሆኑ፣ የዘረኝነት ኣመለካከት የሆኑ፣ የሙስና ኣመለካከት የሆኑ ተግባራትን ስንታገል በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ላይ እንቆማለን ማለት ነው፡፡ እዛ ላይ ሲቆም ዜጎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር፣ ሃብት የማፍራት፣ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታቸው በተሟላ ኣኳኋን ይጠበቃል ማለት ነው፡፡ ያ ካላደረግን በስተቀር ትግሉ ህይወት ሊኖረው ኣይችልም፡፡ ኣሁን  እየሆነ ያለው ግን ሁሉም በየራሱ ብሄራዊ ዋሻ የመደበቅ ነገር ነው እያሳየ ያለው፡፡ መሪያችን ጓድ መለስ ድሮ በፃፋቸው ፅሁፎች ላይ "የመጨረሻ የጥገኛ ሃይሎች ዋነኛ ዋሻ ብሄርና ሃይማኖት ይሆናሉ" ብሎ ነው የሚያስቀምጠው፡፡ ኣሁን በገሃድ እየታየ ያለው እያንዳንዱ "የራሴ ብሄር፣ የራሴ ተወላጅ፣ የራሴ ደም ነው" ይላል፡፡ ከራስህ ብሄር ውስጥ ጠላት እንዳለ የማይገነዘብ ኣስተሳሰብ ነው ያለው፡፡ እኔ ድሮ እስከማውቀው ድረስ በትጥቅ ትግሉ ህወሓት ትግል ሲያደርግ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ፀረ ህዝቦችን ታግሏል፣ ብአዴን የአማራ ተወላጅ የሆኑት ትምክህተኛ ሃይሎች ታግሏል፣ ኦህዴድ የኦሮሞ ጠባብ የሆኑ እንደ ኦነግ የመሰሉ ሃይሎችን ታግሏል፡፡ ዛሬ ይሄ መደባዊ ኣሰላለፍ እየጠፋ "የብሄሬ ልጅ፣ የወንዜ ልጅ" የሚባልበት ሁኔታ እየነገሰ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይሄን የተደበላለቀ ኣስተሳሰብ በመሰረቱ መወገድ መቻል ኣለበት፡፡ ይህንን ሲወገድ ነው በኣብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ኣቋማችን መስመር ላይ ቁመን ሌላውን የድህረት ኣመለካከትና ኣስተሳሰብ መታገል የምንችለው፡፡

 ስለዚህ እያንዳንዱ ድርጅት አሁንም ተድበስብሶ  "ኣንድ ነን" ብሎ የሚመጣ ከሆነ እያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት ኢህኣዴግን ሳያድን እንደገና በዛው ችግር ውስጥ እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡ ከዚህ በኃላ ደግሞ ህዝቡ ሊታገስን ኣይችልም፡፡ ህዝቡ እስከ ዛሬ ድረስ ተስፋው ኢህኣዴግ ነው፡፡ "ኢህኣዴግ የውስጥ ድክመቶቹን አስተካክሎ የኛን ልማት ጥያቄና የመልካም ኣስተዳደር ችግሮቻችንን ይፈታልናል" በሚል በተስፋ እየጠበቀ ነው ያለው፡፡ በየአካባቢው ወጣቶችን ለአመፅ ሲንቀሳቀሱ እንኳን "ተው" እያለ ምክር የሚሰጠው ህዝቡ ነው፡፡ ለምን? ተስፋ ስላደረገ ነው፡፡  "ፌዴራል ስርኣቱ የኛ ነው፤ በዚህ ስርኣት ነው ተጠቃሚ እየሆንን ያለነው፣ ልጆቻችን ትምህርት እያገኙ ያሉት፣ ጤና በአካባቢያችን በየቀበልያችን መጥቶ እየታከምን  ያለነው፡፡ ስለዚህ ይሄን ስርአት ጉድለቶች ቢኖሩበትም እያስተካከልነው ልንቀጥል ይገባል!" የሚል ጠንካራ አስተሳሰብ እና እምነት ስላለው ነው በትእግስት እየጠበቀን ያለው፡፡ ስለዚህ አሁን ወቅቱ ነው፡፡ ወቅቱ አገርን የማዳን፣ ድርጅትን የማዳን እና ህዝባችንን ደግሞ ከገባበት ቀውስ የመታደግ ጉዳይ ስለሆነ እያንዳንዱ ድርጅት የሞት ሸረት ትግል ማካሄድ ኣለበት፡፡ በውስጡ ባሉት አደናቃፊ ሃይሎች ላይ ትግል አድርጎ ጤናማዎችን ወደ አመራርነት የማምጣት፣ የደከሙ አመራሮችን ደግሞ ከሃላፊነታቸው የማውረድ፣ ዝቅ የማድረግ ስራ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ይሄ ለእያንዳንዱ ድርጅት የተሰጠ ተልእኮ ነው፡፡ እያንዳንዱ ድርጅት ይህን እንዲያደርግ ቢጠበቅበትም በዚህ ብቻ ግን እሚያበቃ ኣይደለም፡፡ የኢህኣዴግ ስራ ኣስፈፃሚ ያስቀመጠው ኣቅጣጫ አለ፡፡ እያንዳንዱ ድርጅት የገመገመው ደግሞ በየ 15 ቀኑ  በኢህኣዴግ ስራ ኣስፈፃሚ ተመልሶ ይታያል፡፡ ማነው ስር ነቀል ግምገማ ያካሄደው?፣ ማነው ያልተሟላ ግምገማ ያላካሄደው?፣ ማነው አውሸልሽሎ የመጣው?፣ ማነው በአዳርባይነት ተደራድሮ ያለፈው? የሚለው ይገመገምና በስርኣት ካልገመገመና ስር ነቀል ለውጥ ካላመጣ ድርጅቱ እንደገና መልሶ ውስጡን እንዲመለከት፣ ራሱን መልሶ በድጋሜ እንዲገመግም ይደረጋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ኣይነት መንገድ ትግሉ እየቀጠለ ስለሚሄድ "ሊስተካከል ይችላል" የሚል ተስፋ ይዘን ነው እየቀጠልን ያለነው፡፡ ቁጭትና እልህን ይዘን ስለወጣን   ትግሉ ለውጥ ያመጣል ብለን እናስባለን፡፡ ከዛ በኋላ ደግሞ የኢህኣዴግ ምክር ቤት ተሰብስቦ ሰለሚገመግመው፣ ያሉትን ችግሮችና ለውጦች ስለሚመለከት ለውጡ ይመጣል የሚል ተስፋ ነው ያለን፡፡

ወይን፣ ኢህአዴግ የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማው ካጠናቀቀ በኋላ ባወጣው መግለጫ በኢህአዴግ ብሄራዊ ድርጅቶች አለመተማመን እንደነበረ ከዚህም በተጨማሪ ድርጀቶቹ የጋራ ውሳኔዎች በታማኝነትና በቁርጥጠኝነት የመፈፀም ዲስፕሊን እየላላ እንደመጣ ተገልፀዋል፡፡ የዚሁ መነሻ ምክንያት ምንድነው? ከድርጅቱ የቆየ ታሪካዊ የዲስፕሊን መገለጫወች አያይዘንስ ምን ማለት እንችላለን?

ጓድ ከበደ ፡- እንግዲህ መጠራጠርና አለመተማመኑ እየሰፋ መጥቷል፡፡ የዚህ ትልቁ  መሰረታዊ መንስኤው "ስልጣንን በመጠቀም ራስህን ወደ ጥገኛ ገዥ መደብነት ማሸጋገር፣ የማሸጋገር ፍላጎት እና አመለካከት በየአንዳዱ ኣመራር በመታየቱ ምክንያ ነው" ብለን ነው የገመገምነው፡፡ መንስኤው ይህው ነው፡፡ ይህ ሲባል የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እሴቶች አሉ፡፡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እሴቶች ማለት ምንድናቸው? ያልን እንደሆነ፣ ከሁሉም በላይ ከራስህ በላይ የህዝብን ጥቅም ማስቀደም፣ የአባላትን ጥቅምና መብት ማስቀደም፣ ራስህን ለትግሉ አላማዎች፣ እምነቶች፣ መስዋእት ማድረግ ናቸው፡፡ እነዚህ የኢህአዴግ ዋናዋና እሴቶችና አቅምም አቋምም ነበሩ፡፡ አሁን ግን ይህን ኣስተሳሰብ እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ "ለህዝብ" ከማለት ይልቅ "ለኔ" የሚል አስተሳብ እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ለኔ የሚል አስተሳሰብ እየጎለበተ ሲመጣ ያንተን ጥቅሞ የሚፃረሩ ሀይሎች ሲመጡ መግጠም ትጀምራለህ፡፡  እነዚህ ችግሮች የኛ የዝቅጠት ውጤቶች፣ የኛ ብልሽት የፈጠራቸው ናቸው፡፡ አሁን ያለንበት ምዕራፍ የብዙ ታጋዮች ህይወት ተከፍሎበት የመጣ ነው፡፡ አልጋ በአልጋ ሆኖ የተገኘ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ መርህ እየተጣሰ፣ ህግ እየተጣሰ እየተመለከትን ዝም ብለን የምናይባቸው ገፅታዎች አሉ፡፡ የሰው ሞት፣ የሰው መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት የማይሰማን አመራር እየሆንን መጥተናል፡፡ ቆዳችን እየደነደነ፣  ወፍራም እየሆነ፣ የማንደነግጥ መሪዎች እየሆንን መጥተናል፡፡ ይህ ደግሞ ከግል ፍላጎታችን ጋር ተያይዞ የሚገኝ ችግር ነው፡፡ "ከዚህ መውጣት አለብን" የሚል መሰረታዊ መደምደምያ ሀሳብ ላይ ነው የተደረሰው፡፡ ምንጩ ይህንን ማስወገድ ነው፡፡

ካአሁን በፊት 'የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮች' ተብለው የተቀመጡ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንዱ መሬት ነው፡፡ ሌላው የግዥ እና ኮንትራክት ኣሰተዳደር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የገቢ የታክሲ አሰባሰብ ስርዐታችን ፣ የህገወጥ ንግድ እንቅስቓሴዎቻችን ናቸው፡፡ እነዚህ በሙሉ በድምር ሲታዩ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮች ናቸው ተብለው ተቀምጠዋል፡፡ ሰለሆነም እነዚህን  በአሰራርም በአመለካከትም እያደረቅን አብዮታዊ ስብእናችን ጠብቀን መያዝ መቻል አለብን የሚል ግልፅ የሆኑ ኣቅጣጫዎች ናቸው የተቀመጡት፡፡ እነዚህ ግልፅ ኣቅጣጫዎች ተቀምጠው እያለ ግን እያንዳንዱ አመራር ባለመተማመን ምክንያት የያንዳንዱን እንጀራ የሚያበስልበት መንገድ በመከተሉ ምክንያት እነዚህ የጋራ እሴቶችና ኣቋሞች ሳይዝ እየተደፈጠጠ እየተደፈጠጠ የተሄደበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይህ በመሆኑም የልማታዊነት ፖሎቲካል ኢኮኖሚ እየተዳከመ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል  ኢኮኖሚ ደግሞ በአንፃሩ እየሰፋ፣ እየጠነከረ የሚታገሉ ሃይሎችን ሸባ የሚያደርግበት ገፅታ እየያዘ የመጣ መሆኑ ነው የተመለከትነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ አደጋ በፍጥነት ወጥተን ስርዓቱ፣ ህዝቡንም ድርጅታችንም መታደግ መቻል ኣለብን የሚል የጋራ ኣቋም ነው የተያዘው፡፡

ወይን፣  የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች በሚከተሉት ፖለቲካዊም ሆነ ፖሊስና ስትራተጂ አልያም አገሪትዋ በምትተዳደርበት ፌደራላዊ ስርዓት ልዩነቶች የላቸውም፤ ኢህአዴግ እንደሚለውም እነዚህ ብሄራዊ ድርጅቶች የአስተደደር ቅርፅ ከመወከላቸው ውጭ በሁሉም አንድ ናቸው፡፡ ይህንን ስናስብ፣ በተለይ ህወሓትና ብአዴን እንደዚሁም የትግራይና የአማራን ህዝብ በጋራ የከፈሉት መስዋእት ደግሞ አለ፡፡ ይህ  ሆኖ ሳለ በነዚህ ድርጅቶች መሀከል አለመተማመንና ልዩነት እንዴት ሊፈጠር ይችላል?

ጓድ ከበደ፡- እንደተገለፀው ብአዴንና ህወሓት በደም የተሳሰረ አንድነት ነው ያላቸው፡፡ ከመጀመርያው ጀምሮ ብአዴን ገና ኢህዴን በነበረበት ጊዜ፣ ከኢህአፓ ተገንጥሎ ድርጅት ለመምስረት ሲንቀሳቀስ ጥላ ከለላ ሆኖ ያገለገለው ህወሓት ነው፡፡ ያኔ ኢህኣፓ ግዙፉ ድርጅት ነበረ፡፡ ግን የጠራ መስመር ኣልነበረውም፡፡ ውስጠ ዴሞክራሲያዊ ባህል ኣልነበረውም፡፡ የገጠርን የትግል ስልት እንደኣማራጭ የማይመለከት ድርጅት ነው የነበረው ኢህአፓ፡፡ በዚህ ምክንያት በውስጣዊ ችግሮች ምክንያት ተፈረካክሶ ግማሹ ለደርግ ሲንበረከክ፣ ግማሹ ወደ ውጭ ወደ ስደት ሲሄድ፣ ጥቂቶቹ ደግሞ "ጭቆና እስካለ ድረስ ትግል ኣይቀሬ ነው ብለው ሲታገሉ መጠለያ፣ ከለላና መከታ ሆኖ ያገለገላቸው ህወሓት ነው፡፡ ህወሓት ይብዛም ይነስም የተሻለ ብሄራዊ ትግልን የሚያንቀሳቅስ ድርጅት ስለነበረ መጠለያ ሆኖ ኣገልግሏል፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ  ህወሓትና ኢህዴን በጋራ ዓላማ ዙርያ ተሰባስበው ህዝባቸውን እያታገሉ የጋራ እቅድ እያቀዱ ተንቀሳቅሰው በደም የታሳረ ግንኙነታቸውን ገንብተው የመጡ ድርጅቶች ናቸው፡፡

ለእኔ የብአዴንና የህወሓት ትስስር በዚህ ብቻ የሚገለፅም መስሎ ኣይታየኝም፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ኣብዮት ታሪክ ውስጥ የከፈሉት ዋጋ፣ ያበረከቱት ኣስተዋፅኦ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢህዴንም  ያኔ መታገያ ያልነበራቸው ህብረብሄሮች፣ ከሁሉም ብሄር የተውጣጡ ወጣቶችም ጭምር መታገያ መድረክ በመሆን ኣገልግሏል፡፡ ለኦህዴድ መመስረትም፣ ለኦህዴድን መመስረትም የበኩሉ ኣስተዋፅኦ ኣድርገዋል ኦህዴን፡፡ ስለዚህ የብአዴንና  የህወሓት እህትማማችነት አሁን የተፈጠረ ኣይደለም፡፡ ገና በጥዋቱ ግልፅ ኣቋም ይዘው ብአዴን የጭቁኑን የአማራ ህዝብን ከጎኑ ኣሰልፎ የአማራ ገዥ መደቦችን ለመታገል ቆርጦ የተነሳ ድርጅት ነው የነበረው፡፡

ምክንያቱም የአማራ ህዝብም ቢሆን ከአማራ ገዥ መደቦች ያገኘው ጥቅም አልነበረም፡፡ የአማራ ህዝብ መቼም ቢሆን ተጠቃሚ ኣልነበረም፡፡ ግን በሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ኣይን ሲታይ የአማራ ህዝብ እንደ ጨቋኝ ኣድርጎ የሚያይ አለ፡፡ እንደ ነፍጠኛ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ነፍጠኞቹና ገዢ መደበቹ የአማራ ጥቂት ገዢ መደበች ናቸው የነበሩት፡፡ ሰፊው የአማራ ህዝብ ግን እንደሌላው የኢትዮጵያ ብሄርብሄረሰብ ህዝብ ተጨቋኝ የነበረ፣ ያመረተውን ምርት በግድ እየተነጠቀ የሚወሰድበት፣ በድህነት ኣዙሪት ውስጥ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ ለዚህ ህዝብ መድን ሆኖ ኢህዴን ሲታገል፣ ብአዴን ሲታገል ብቻውን አልነበረም፡፡ ከህወሓት ታጋዮች ጋር ኣብሮ አንድ ምሽግ ላይ እየወደቀ የታገለ ድርጅት ነው፡፡ ይሄ ብቻም ኣይደለም፡፡ የህወሓት ታጋዮች ሲመጡ የአማራ ህዝብም ደግፎዎቸዋል፡፡ አብሮ ኣብልቶ፣ ኣጠጥቶው "ኣይዛችሁ በርቱ" ብሎ ከታጋዮቹ ጎን በመሆን ኣታግሏል፡፡

እኔ በጣም ውስጤ የሚሰማኝ ጉና ተራራ ላይ ከባድ መስዋእትነት ሲከፈል  ትግራይ ሙሉ በሙሉ ነፃ ወጥቶ ነበር፡፡  ትግራይ መቶ "ፐርሰንት" ነፃ በወጣበት ጊዜ የህወሓት ታጋዮች "ትግራይ  ነፃ ወጥታለችና ከዚህ በኃላ እኛ ደክሞናል ሌላው ህዝብ ደግሞ ትግሉን ይቀጥል፡፡ እኛ ራሳችን ነፃ እስካወጣን ድረስ ይበቃናል" የሚል ጥያቄ ታጋዮቹ ነበራቸው፡፡ "ጥያቄ ነበረቻው" ብቻ ሳይሆን ከሀያ ሺ ያላነሰ ታጋይ "በቃን" ብሎ ወደ ትግራይ ተመልሶ ነበር ያኔ፡፡ ደርግ ሳይደመሰስ በተመለሰበት ጊዜ ህወሓት ምንድነው ያደረገው? "የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ለሙሉ ነፃ ሳይወጣ፣ ትግራይ ነፃ ሊወጣ ኣይችልም፤ ስለሆነም የትግራይ ህዝብ ተመልሰው ወደ ቤት የመጡ ልጆቻችሁን መክራችሁ እንደገና ወደ ትግሉ፣ ወደ ጦርነት ኣውድማው ላኩ" ብሎ "ዕሰልየ፣ ዕሰልየ፣ ኣቦኻ ምሰልየ" (እንደ ኣባትህ ዝመት … ዝመት) እየተባለ እንዲቀሰቀስ ተደርጎ እንደገና  እነዛ ታጋዮች ወደ ሰራዊታቸው  ተመልሰው እንዲታገሉ ተደርገዋል፡፡ ያኔ ህወሓት ጠባብነት ቢኖረው፣ ህወሓት ለዲሞክራሲ አንድነት የማይታገል ድርጅት ቢሆን ኖሮ "ትግራይ ነፃ ወጥታለችና ትግሉ ይበቃል" ማለት ይችል ነበር፡፡ ግን ኣላለም፡፡ ህወሓት ልጆቹን መክሮ "የኢትዮጵያ ነፃነት ሳይከበር፣ የኢትዮጵያ ነፃነት ሳይረጋገጥ ትግራይ ነፃ ልትወጣ ኣትችልም፡፡ ስለሆነም ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ወንድሞቻችን ጋር ሆነን እንቀጥላለን፤ ቀጥሉ" ነው ያላቸው፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፡፡ ደርግም ከተደመሰሰ በኃላ የኢትቶጵያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰብ መምሰል ስለነበረበት ብሄራዊ ተዋፅአውን ለማመጣጠን ሲባል ህወሓት ትልቅ ስራ ሰርቷል፡፡ በታሪክ ኣጋጣሚ በጣም በርካታ ሰራዊት የነበረው ህወሓት ነው፡፡ ቀጥሎ ኢህዴን ነው፡፡ ቀጥሎ ኦህዴድ ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በጣም ትንሽ የዴህደን ነው የነበረው፡፡ ስለዚህ ብዙ ሰራዊት የነበረው ድርጅት ህወሓት ስለነበረ "ባበረከትኩት ትግል ልክ፣ በከፈልኩት መስዋእትነት ልክ መጠቀም ኣለብኝ" ኣላለም፡፡ ወይም የተለየ ጥቅም ይገባኛል ብሎም ጥያቄ ኣላነሳም፡፡ ምንድነው ያደረገው ህወሓት? የኢትዮጵያ ሰራዊት  ብሄራዊ ተዋፅኦ የተመጣጠነ እንዲሆን የትግራይ ተጋዮች፣ የህወሓት ታጋዮች በክብር ተቀንሰው፣ ኣንድ ሺ አምስት መቶ እየተሰጣቸው ኣርሰው እንዲበሉ ወደ ትግራይ እንዲመለሱ ነው የተደረገው፡፡ ይሄ ከመብት አንፃር ካየነው እነዚህ ታጋዮች ታግለዋል፤ አገርን ነፃ አውጥተዋል፡፡ መጠቀም ነበረባቸው፤ ደመወዝ ማግኘት ነበረባቸው፡፡ ግን ከስንት ትግል በኃላ "ሂዱና አርሳችሁ ብሉ፤ ብሄራዊ ተዋፅኦ ለማመጣጠን የሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ልጆች በሰራዊቱ ውስጥ መግባት ኣለባቸውና ውጡ" ነው የተባሉት፡፡ ያኔ ወጥቷል፡፡ አንድ ሺ ኣምስት መቶ ብር መሳፈርያ እየተሰጣቸው ነው የሄዱት፡፡ ያን ሁሉ ልፋት ለፍተው አገር ነፃ አውጥተው አሁን በጉስቁልና የሚኖሩ በርካታ ታጋዮች አሉ፡፡ ስለዚህ ህወሓት ከማንም በላይ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ፌዴራላዊ ስርዓት እንዲኖር፣ ልጆቹን የገበረ ድርጅት ነው ለኔ፡፡ ልጆቹን የገበረ ድርጅት ነው ህወሓት፡፡

ከዛ በኃላም ህወሓት በተለየ መንገድ "የበላይ" እንዲሆን፣ "የትግራይ ህዝብ የበላይነት እንዲረጋገጥ" የሰራው አንድም ስራ የለም፡፡  በደርግ ጊዜም ወንበዴና ገንጣይ አስገንጣይ ሲባል ነበር፡፡ ከዛ በኃላም  ጠላቶቻችን ይህንን "እኝኝ" ብለው የቀጠሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የትግራይ ህዝብ ዛሬም ቢሆን በጥፍሮቹ ከተራራ እየታገለ በሚኖርበት ሁኔታ ላይ ግን "የትግራይ ህዝብ የተለየ ጥቅም እንዳገኘ፤" "የህወሓት የበላይነት በዚች አገር እንደተረጋገጠ" ይሰበካል፡፡ "ሶሻል" ሚድያውም ይህንን ተቀብሎ ያስተጋባል፡፡ ሌላውም የራሱን አመለካከት ኣድርጎ ይወስዳል፡፡ ግን እውነታው እንደሱ ኣይደለም፡፡ እውነታው በአገራችን ውስጥ  ሁሉም ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ፤ በጀት በቀመር ይከፋፈላል፡፡

ይህ ሆኖ ሳለ ታድያ ለምድነው በህወሓትና በብአዴን አለመተማመን ልዩነት የተፈጠረው ካልን ግን የጎራ መደበላለቅና የአብዮታዊነት ጉድለት እየገዘፈ በመምጣቱ ነው፡፡ ወይም በትምክህት ወይም በሌላ ምክንያት ህወሓትን በጥርጣሬ ዓይን የሚያይ ኣመራርና አባል እየሰፋ በመምጣቱ ምክንያት የጎሪጥ ለመተያየት ምክንያት ሆነዋል፡፡ ኣመራሩ ላይ ያለው የተዛባ አመለካከት ወደ ህዝቡም እየተሰተጋባ በክልሉ  ለዓመታት የኖሩ የትግራይ ተወላጆች በጥርጣሬ እንዲታዩ ወይም ንብረታቸው እንዲዘረፉ፣ እንዲቃጠሉ ወይም እንዲወጡ የተደረገባቸው ኣጋጣሚዎች አሉ፡፡ ለኔ ይሄ በብአዴን ታሪክ፣ በአማራ ህዝብ ታሪክ ጥቁር ነጥብ ነው፡፡ ህወሓትና ኢህዴን፣ የአማራና የትግራይ ህዝብ በደም፣ በባህል በአድነትና በደም የተዋሀደና የተሳሰረ ህዝብ ሆኖ ሳለ ግን ደግሞ ሁለቱንም ህዝብ ሊያራርቅ የሚችል ስራ መስራት ለኔ የታሪክ ጥቁር ነጥብ ነው ብየ ነው የማስበው፡፡ ከንደዚህ ኣይነት ሁኔታ ተሎ መውጣት ኣለብን ብየ አስባለሁ፡፡ "ዛሬም የትግራይ ተወላጅ የሆነ ሰው እየተፈለገ ንብረቱ የሚዘረፍበት፣ ቤቱ የሚቃጠልበት ሁኔታ የአብያታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ውጤት ሳይሆን የትምክህትና የዘረኞች ኣስተሳሰብ ውጤት ነው" ብየ ነው የማምነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ኣኳያ በነዛ ጠላት ሀይሎች ላይ ጠንካራ ትግል ያስፈልገናል እላለሁ፡፡

ወደ ኃላ ተመልሰን ማየት ያስፈልግ እንደሆነ የሁለቱ ድርጅቶች መሳሳብ መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ነበሩ፡፡ እንደዚህ አይነት አጋጣሚ ሲፈጠር ሁለቱም ድርጅቶች ችግሮችን ተሎ ያለመፍታት ችግር ነበረ፡፡ ከዚህ ኣኳያ የሚነሳው አንዱ የግጨው ጉዳይ ነው፡፡ የግጨው ጉዳይ ለእኔ የሀያ ሺ ሄክታር መሬት ጉዳይ ነው፡፡ ሀያ ሺ ሄክታር መሬት ወደ ትግራይ ቢሄድ፣  ወደ አማራ ቢመጣ ህወሓትና ብአዴን የሚያጣላቸው መሆን የለበትም፡፡ ሀያ ሺ ሄክታር መሬት አንድ ባለ ሀብት በኢንቨስትመንት መልክ የሚወሰደው መሬት ነው፡፡ በደም ተሳስረው ረጅም የትግል ውጣ ውረድ ኣሳልፈው የመጡ ድርጅቶች በሃያ ሺ ሄክታር መሬት ተጣልተው አመራሩን ጭምር በዚሁ ላይ የልዩነት አቋም ይዞ ህዝቡን የምያቅቅር  ስራ መስራት ነበረባቸው ብየ አላምንም፡፡ ህዝቡን እንዲፈራቀቅ ያደረጉት የአመለካከት ብልሽታቸው ውጤት ነው፡፡ ኣብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ባለመያዛቸው የተፈጠረ ነው፡፡ እይታችን ሁለቱንም ህዝቦች የሚጠቀሙበት ሳይሆን እይታችን መሬት በመሆኑ ነው፡፡

ደርግም እኮ ድሮ የነበረው መፈክሩ "ኤርትራ ከሄደች አንገታችን ይቆረጣል" ነው፡፡ የኤርትራ ህዝብ ወደዚህ የማምጣት ፍላጎት ኣልነበረውም፡፡ "የኤርትራ መሬት ለምን ይሄዳል?" ነው፡፡ "የባህር በራችን ለምን ይሄዳል?" ነው፡፡ እኛ ያኔ መፈክራችን የግዛት አንድነት ሳይሆን የዝህቦች አንድነት ነው የነበረው፡፡ የህዝቦች አንደነት ከሆነ ግጨው ላይ ስንመጣ የሁለቱንም ህዝቦች ከሆነ የሚያሳስበን መሬት ላይ ለምን እንመለከታለን? መሬቱ የገዥዎች ኣስተሳሰብ ከሆነ ለምን መሬት ላይ ትኩረት አደረግን? አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ኣስተሳሰብ ደግሞ ህዝቦችን ነው የሚያየው፡፡ ህዝቦች በጋራ ይኑሩ፤  እዛ ሀያ ሺ ሄክታር ላይ የሚኖረው አርሶ አደር እስካልተፈናቀለ ድረስ ከመሬቱ ልቀቅ እስካልተባለ ድረስ ምንም የሚያጣላው ነገር የለም፡፡ አስተዳደሩ ቢፈልግ ወደ ትግራይ ሊሆን ይችላል፤ ቢፈልግ ወደ አማራ ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም ሀጥያት የለውም፡፡ ዋናው ህዝቡ መልካም አስተዳደር ማግኘቱ ነው፡፡ ይሄ ሆኖ እያለ እኛ ግን እንደ አመራር ተከፋፍለን የልዩነት ነጥብ ሆኖ ከሀያ ኣመት ያላነሰ ጊዜ ሲጓተት ቆይቷል፡፡ ኣመራሩ ትኩረት መሰጠት ነበረበት፡፡

ሁለተኛ ደግሞ ኣመራሩን ጉዳዩን በፍጥነት መፍታት ነበረበት፡፡ ለመፍታት ሲሞክርም በመሬት መሳሳብ ምኽንያት "እቺ ወደዚህ፣ እቺን ወዲዚያ" እያለ ረጅም ጊዜ ሲያጓትተው ቆይቷል፡፡ ይሄ ቁርሾ በብአዴንና በህወሓት መሀከል የበለጠ እንዲሰፋ ኣድርጎታል፡፡  ይሄ አንድ ነው፡፡ ሁለተኛው ከዚህ ከወልቃይት ከምንም ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ጥያቄ ካለ ህገ-መንገስታዊ ጥያቄውን ኣቅርቦ ሊመለሰለት ይችላል፡፡ ጥያቄ  ከሌለውም በዛ የሚያበቃ ነገር ነው? ኣይደለም፡፡ ለሌሎች የትምክህት ሃይሎችና ፀረ ሰላም ሃይሎች መንጠላጠያ ገመድ ሆኖ እንዲያገልግላቸው ግን በር ከፍተናል፡፡  እኛ በራሳችን  በር ነው የከፈትነው፡፡ ይህንን በደምብ መታየት መቻል ኣለበት፡፡

ሌላው ችግር የሚፈጥረው ህወሓትን ወይም የትግራይ ህዝብን እንዲጠላ የሚያደርጉ የትግራይ ተወላጆች አሉ፡፡ ጥገኛ የሆኑ ሃይሎች አሉ፡፡ እነዚህም ህወሓት መታገል ነበረበት፡፡ ሁላችንም መታገል ነበረብን፡፡ በእኔ እምነት ድሮ ደርግ በነበረበት ጊዜ የትግራይ ተወላጆችን "የወያኔ ሰላዮች ናቸው፣ የወያኔ ስምሪት ናቸው" እያለ የሚያስጨፈጭፍ የነበረ ሰላይ የትግራይ ተወላጅ ነው፡፡ ልክ ያኔ እንደዛ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም "ስርዓቱ የኔ ነው" እያለ የሚያስፈራራ፣ "ስርዓቱ የኔ ነው" እያለ የራሱን ጥቅም የሚያሳድድ ጥገኛ የትግራይ ተወላጅ አለ፡፡ በተለይ በዚህ በአዲስ አበባ ዙርያ ብዙ ጥገኛ አለ፡፡ ይህንን ጥገኛ ሀይል መታገል አለብን፡፡ ይሄን ሃይል ነው ህወሓትን እንዲጠላ፣ የትግራይ ህዝብ እንዲጠላ እያደረገ ያለው፡፡ ብረት ያስመጣል አየር በአየር ይሸጣል፡፡ "አለማለሁ" ብሎ የእርሻ መሬት ይወስዳል፣ እርሻውን ሳያለማ ወደ ሪልስቴት ግንባታ ይገባል፡፡ ግብር መክፈል እየተገባው አጭበርብሮ ይሄዳል፡፡ ከባንብክ ብድር ይወስዳል ሳይሰራ ያጠፋፋል፡፡ ሲጠየቅ በትግራዋይነቱ ያስፈራራል፡፡ ስለዚህ ሌላው ብሄረሰብ ምንድ ነው የሚያየውና የሚያስበው? የእውነት የትግራይ ህዝብና ህውሓት ከጀርባቸው እንዳለ ያስባል፡፡ "ስርዓቱ እማ የነሱ ነው፡፡ ስለዚህ እነሱን ብንናገር ነገ ልያሳስሩን ይችላሉ" ብሎ በመስጋት ይፈራቸዋል፡፡ እንደዚህ አይነት አመለካከት አለ፡፡ ይሄን አመለካከት መቀየር ኣለብት፡፡ እዚሁ ያለው ጥገኛ ትግራዋይም ይሁን ጥገኛ አማራ፣ ጥገኛ ጉራጌም ይሁን ጥገኛ ስልጤም ሁሉም "ጥገኛ ጥገኛ" ነው፡፡ በስርዓቱ፣ በልማታዊ መንገዱ ሄዶ እስካልሰራ ድረስ፣ በጥገኝነት መንገድ እስከተጓዘ ድረስ ዞሮ ዞሮ ጥገኛው የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችንን ሁልውና የሚፈታተን ነው፡፡ ስለሆነም  ከሁሉም በላይ እያንዳንዱ ድርጅት የራሱን ጥገኛ ሀይል መታገል ኣለበት፡፡

ቀጥሎ ደግሞ የሌላውን ጥገኛ በአንድነት መታገል መቻል አለበት፡፡ ስለዚህ ህወሓት ይሁን ብአዴን የደከሙበትን  አንዱ ገፅታ ጥገኛ ሃይሎችን ከመታገል ይልቅ የራሳቸው ብሄር ተወላጅ  አቅፈው መያዛቸውም ጭምር  ነው፡፡ ይህንን ህወሓትም በራሱ በዝርዝር የገመገመውና "ከዚህ በኋላ መታገል አለብን" ብሎ ያለው ጉዳይ ነው፡፡

ስለዚህ ይሄን አመለካከት በትክክል ከተስተካከለ የትግራይ ህዝብ የተለየ ጥቅም እንዳላገኘ ህወሓትም የበላይነት በዚች አገር ውስጥ ያልገነባ መሆኑ በጋህድ የሚታይበት ሁኔታ ይኖራል ብየ ነው የማስበው፡፡ በዚህ ቅኝት ነው መታየት ያለበት፡፡ በህወሓትና በብአዴን ላይ የነበረው መፈራቀቅ ዛሬ መለወጥ በመጀመራችን፣  በተሃድሶ ሂደት በማለፋችን ምክንያት የግጨው ጉዳይ በቀላሉ ተፈቷል፡፡ ሌላም ቢሆን አንድ የሚያጣላን ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ ቢያንስ በአንድነታችን ላይ የተፈጠረው መጠራጠርና ኣለመተማመን እየተፋቀ ወደ አንድ የምንመጣበት መንገድ ስለፈጠርን አሁን በእርግጠኝነት በህወሓትና በብአዴን መካከል የነበረው አንድነት ወደ ድሮው ወደ ነበረበት ጠንካራ አንድነት ተመልሶ አንድነታችን ጠብቀን እንሄዳለን የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡

ወይን፣ ኢህአዴግ ግምግማውን ካጠናቀቀ በኋላ በድክመቶቹ ምክንያት ለተፈጠሩ ችግሮች ለህዝቡ በኢፋ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ችግሮቹ ወደፊት ዳግም ላለመከሰታቸው አሁን ሆነን ምን ያህል እርግጠኛ መሆን እንችላለን?

ጓድ ከበደ፣ እንግዲህ ተስፋችን አሁን  በስራ ኣስፈፃሚ ደረጃ የተደረገውን ትግል ላይ ፍፁም መተማመን የተፈጠረበት፣ ጥርጣሬውን ያስወገደና ጥሩ መንፈስ ተይዞ  የተወጣበት ነው፡፡ ይህን ይዘን ወደ ማእከላይ ኮሜቴው ስንወርድ  ደግሞ የበለጠ አቅም እንፈጥራለን፡፡ አቅም የምንፈጥረው በመውሸልሸል አይደለም፡፡  እውነታዎች ላይ ፍርጥርጥ ብለው ወጥተው በመተማመን ነው፡፡ በመተማመን ላይ የተመሰረተ ትግል ስናካሂድ ደግሞ የበለጠ አቅምና ጉልበት እየሆነን ይሄዳል፡፡ ይህን ጉልበት ይዘን ወደ ኣባላት ወደ ህዝቡ ስንወርድ የበለጠ ጉልበት እናገኛለን፡ ልክ የዛሬ 15 ዓመት እንደነበረው ተሃድሶ ወደፊት የሚያስፈነጥረን ነው የሚሆነው፡፡ ወደ ኃላ የሚመለስ ኣይሆንም፡፡ ትግላችን ኣዳክመነው ኣውሸልሽለን የምናልፍ ከሆነ ግን አሁንም መደባበቁ ካለ መሸዋወዱ ካለ "በጥልቀት እንታደሳለን" ብለን ደግሞ እንደገና መልሰን ልንዘቅጥ እንችላለን ማለት ነው፡፡ አሁን መልሰን ከዘቀጥን መቼም ቢሆን መዳኛ የለምን፡፡ ይሄ ህዝብ አንድ ዕድል ብቻ ነው የሰጠን፡፡ ይሄ ዕድል ለኢህኣዴግ ወይ መሞት ወይ መዳን ነው፡፡ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ወይ በዚህ መድረክ ድነን በፍጥነት እንወነጨፋለን ወይም ደግሞ መዳን አቅቶን ሙተን ህዝባችን ለእልቂት፣ አገራችን ደግሞ ለብተና ልንዳርጋት እንችላለን፡፡ በዚህ ቋንቋ ነው የተነጋገርነው፡፡

ስለዚህ ጉዳዩ የመዳንና ያለመዳን ጉዳይ፣ አገርን ወደ ፊት የመውሰድ ያለመውሰድ ጉዳይ ተሃድሶውን የማስቀጠል ያለማስቀጠል ጉዳይ ስለሆነ እያንዳንዱ ድርጅት የሚያካሂደው ትግል የሞት ሽረት ትግል ነው፡፡ እኔ አንተን ስለማውቅህ ተደራድሬ ማለፍ የለብኝም፡፡አንተ እኔን ስለምታውቀኝ ተደራድረህብኝ ልታልፍ ኣይገባም፡፡ ያሉንን ችግሮች በሙሉ አፍረጥርጠን ተወያይተን ተማምነንባቸው ከዚህ በኋላ የአመለካከትና የተግባር አንድነት ፈጥረን በጋራ የሃላፊነት ስሜት ከገባንበት ማቅ ለመውጣት መስራት አለብን የሚል እምነት ነው የተያዘው፡፡ በዚህ እምነት ደረጃ ውይይት ስለተደረገ ተስፋችን ከችግሩ ወጥተን የህዝቡን አንገብጋቢ ጥያቄዎች፣ የልማት ጥያቄዎች እንፈታለታለን የሚል እምነት ተይዞ ነው እየተሰራ ያለው፡፡ አሁንም ከዛ ስራ ኣስፈፃሚ መድረክ በኋላ ከ12 ያላነሱ ንኡሳን ኮሚቴዎች ተደራጅተው በእያንዳንዱ ችግሮች ላይ የሪፎርም ስራ ለማካሄድ እየተሰራ ነው ያለው፡፡ ኮሚቴዎች እየሰሩ ናቸው ያሉት፡፡ የፀጥታ ኮሚቴ አለን፣ ተፈናቃዮችን የሚያቋቅም ኮሚቴ አለን፣ የኮንትሮባንዲስት ችግሮች የሚመለከት አለ፣ የሚድያ ስራዎች የሚከታተል ኮሚቴ ወዘተ አለ፡፡ በአጠቃላይ ስራ አስፈፃሚው በጋራ ስምረት  እየሰራ ነው ያለው፡፡ ይህንን ስራዎች የምንሰራው ከችግሮቻችን ለመውጣት ባለን ፍላጎት ነው፡፡ ስለሆነም እነዚህን ደግሞ ሌተቀን ከልብም ሰርተን ከተለወጥንባቸው ኢህአዴግ ወደ ፊት ይወነጨፋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ኢህአደግ በታሪኩ ብዙ ጊዜ ከችግሩ እስኪነቃ ድረስ ያንቀላፋል ግን ካንቀላፋ በኃላ ተነስቶ ወደ ፊት ሲሄድ ተአምር የሚሰራ ድርጅት ነው፡፡ እኔ ባወቅኩበትና በታገልኩበት ዘመን የማውቀው ኢህአዴግ ይህንን  ነው፡፡ ህወሓትም ታሪኩ ይህንን ነው፡፡ ህወሓት ድሮ በ1977 ዓ/ም መስመሩን ሲያጠራ በጣም ምርጥ መፎክር ነበረው፡፡ የቻለ ይሩጥ፣ ያልቻለ ያዝግም፣ የተሸከለ ደግሞ ይወገድ የሚል መፎክር ነበረው፡፡ ያ መፎክር መስመርን ኣጥርቶ ህወሓት ወደፊት እናዲወነጨፍ ነው ያደረገው፡፡ እስከዛ ድረስ ግን ህወሓት አንቀላፍቶ ነበር፡፡ ያ መስመር አጥርቶ ወጥቶ ወደ ፊት ሲሄድ ግን ወደ መሃል አገር እንዲፈነጠር፣  ከብአዴን ጋር ሆኖ እንዲገሰግስ እድል ሰጥቶታል፡፡ ከደርግ ድምሰሳ በኃላም በ1985 ኮንፈረንስ ሲካሄድ ህወሓት ላይ ግለኝነቶች ብቅብቅ ማለት ጀምረው ነበረ፡፡

ድሮ (በትግል ወቅቱ ማለቴ ነው) "ከየት ወዴት" የሚል ፅሑፍ ነበረን፡፡ "ከየት ወዴት" የሚለው ፅሑፍ መንግስታዊ ስልጣን ስንይዝ፣ ወደ ከተማ ስንገባ የኢኮኖሚ ማማረጥ ሊያገጥመን ይችላል፡፡ የኢኮኖሚ ማማረጥ ማለት አሁን "ጥገኝነት" ብለን የምንለው ወይም "የጥገኛ ዝቅጠት አደጋ" ብለን የምንለው ነው፡፡ ያኔ በኢኮኖሚ ማማረጥ ነበረ የምንገልፀው፡፡ "ያ አደጋ ሊያጋጥመን ይችላል" በሚል ተገምግሞ ተተምብዮ ስለነበረ ያ ትምቢት በ1985 ዓ/ም በህወሃት ተጋዮችም፣ አባላትም ፣ ኣመራርም አከባቢ መከሰት ጀመረ፡፡ ያኔ በነ ታምራት ላይኔ ጋርም መከሰት ጀመረ፡፡ በነ ስየ አብርሃ መከሰት ጀመረ፡፡  ያኔ ምንድነው የተደረገው?  አሁንም የቻለ ይሩጥ፣ ያልቻለ ያዝግም፣ የተሸከለ ይወገድ የሚለው መፎክር አንግቦ ሲነሳ ብዙ ሰው በጥርጣሬ አይን ተመለከተው፡፡ "ለምን ዝም ኣላችሁ?" "ኣይ! መፎክር ኣይተን ነው ዝም ያልነው?" ተባለ፡፡ ይህ መፎክር ግን ህወሃትን ወደ ፊት ወስዶታል ኣልወሰደም ታድያ ለምንድነው የተነካካ ሰው ፍርሃት ስለነበረው ኣለቀሰ መጨረኻይ ታግሎ ግለኝነት ውስጥ የገቡትን በጥገኝነት እና በክራይ ሰብሳቢነት ኣመለካከትና ተግባር ታግለው ለማስተካከል ዕድል ኣገኘ፡፡ ቀጠለ እንደገና! ብአዴንም በተመሳሳይ መንገድ "የከፉ ጫፎች ይወገዱ" የሚል ነገር ነበረው፡፡ ለስርዓቱ፣ ለትግሉ፣ ለመስመሩ እንቅፋት የሆኑ ሀይሎችን ይወገዱ፡፡ ከመስመሩ ገለል ይበሉ፡፡ የመስመሩ ሀይሎች ደግሞ ትግሉን ይዘው ወደ ፊት ይግፉ የሚሉ መፎክሮች ነበሩት፡፡ እነዚህ መፎክሮች ወደ ፊት ነው እንጂ የወሰዱን ወደ ኃላ ኣልጎተቱንም፡፡  ኢህኣዴግ  የዛሬ 15 ዓመት በ1993 ዓ/ም ተሀድሶ ሲያደረግ "የጥገኝነት አደጋ በውስጣችን ሆኖ እያስቃየን ነው፤ ከዚህ መውጣት ኣለብን" ነው ያለው፡፡ ከዛ ወጥተንም ለ15 ዓመታት ተከታታይ እድገት እንዲመዝገብ ተአምራዊ ለውጥ እንዲመጣ ያደረገው በኢህኣዴግ ግንባር ቀደም መሪነት ነው፡፡

 ለምን? ቢባል፣  ያኔ የነበረው አመራር የመበስበስ አደጋው ታግሎ በማስተካከሉ ምክንያት የመጣ ለውጥ ነው፡፡ ስለዚህ የኢህኣዴግ ልምዶች እና ተመክሮዎች ተጨምቆው ሲወሰዱ ኢህኣዴግ ራሱን በራሱ ማረም የሚችል ድርጅት በመሆኑ፣ ስህተቱን ወደ ሌላ አካል የማይወረውር (Extrnalize የማያደረግ) ድርጅት በመሆኑ ሁሌ ውስጣዊ ችግሩ በገመገመ ቁጥር ከችግሩ የመውጣት ተስፋ ይዞ የመጣ ድርጅት መሆኑ ነው የምንረዳው፡፡ ስለዚህ አሁንም ያደረገው ነገር ምንድነው? ተቋዋሚዎች ናቸው እንዲህ ያስናከሉኝ አላለም፣ በእርግጥ ፀረ ሰላም ሀይሎች ስለማይሰሩ አይደለም ይሰራሉ ሌተቀን ይሰራሉ፡፡ በህጋዊ መንገድ እንንቀሳቀሳለን ያሉትም ይሁኑ፣ ትጥቅ ታጥቀው ስርዓቱ ለማፍረስ የሚሯሯጡትም ይሁኑ  የኤርትራ መንግስትን ጨምሮ ሌሎችም ሃይሎች እኛ ላይ የማይሰሩት ስራ የለም፡፡ ግን "ጠላት ስለጠነከረብኝ ነው እንዲህ የሆንኩኝ" አላለም ኢህኣዴግ፡፡ "የውስጤን ድክመት በማስተካከል ነው፤ ፀረ ሰላም ሀይሎችንም መንጠላጠያ ገመድ የማሳጣቸው" ብሎ ነው እየታገለ ያለው፡፡ ስለዚህ ሁሌ ራሱን በራሱን ማረም የሚችል ጠንካራ ድርጅት  ነው ኢህኣዴግ፡፡ ልምዱን የሚያሳየው ይህ ስለሆነ ይመስለኛል ከዚህ በኃላ የዘቀጠ ህይወት ውስጥ እንገባለን የሚል እምነት የሌለኝ፡፡

ወይን፣ ኢህአዴግ የአሁኑ መድረክ ከመካሄዱ በፊት ራሳቸውን ማየት የቻሉ እህት ድርጅቾች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሌሎች ደግሞ ይህን ማድረግ ኣልቻሉም፡፡ የዚህ መንስኤ ምንድነው ማለት እንችላለን? ከዚህ ጋር ተያይዞ "ብሄራዊ ድርጅቶች ችግሮቻቸውን ፈትተው ይወጣሉ ወይ?" የሚሉ ጥርጣሬዎች ኣሁኑም ይታያሉ፡፡  በዚህ ዙርያ ብአዴን ኢህኣዴግ ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ እንዴት ልንገመግመው እንችላለን?

ጓድ ከበደ፣  ያው ቅድም ገልጭዋለሁ፡፡ "ዘሮ ዘሮ ሁሉም (አራቱም) ብሄራዊ ድርጅቶች ችግሮቻቸውን ገምግመው የተስተካከለ ኣቋም ይዘው ይወጣሉ" የሚል ተስፋ ነው ያለው፡፡ ብአዴንም በተመሳሳይ መንገድ ያሉበትን ችግር ገምግመዋል በሰፊው፡፡  በመጀመርያው የጥልቅ ተሀድሶ ጊዜ ገምግሞ እስከ ታች ድረስ ለመውረድ መኩረዋል፡፡ የተሻለ ለውጥ ማምጣትም ተጀምረዋል፡፡ ግን ደግሞ አሁንም ያልተሻገርናቸው ችግሮች አሉ፡፡ ያልተሻገርናቸው ችግሮች ምንድ ናቸው? ከጎራ መደበላለቅ ጋር ተያይዞ፣ "የአማራ ህዝብ ፍትሓዊ ተጠቃሚ አልሆነም" የሚል አስተሳሰብ ጎልቶ የሚታይበት፣ "አማራ ተበድለዋል" ተብለው የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እዚህ ላይ የታየና በኢህአዴግ ስራ ኣስፈፃሚ ደረጃም መተማመን የተደረሰበት ምንድነው? የአንድ ክልል ሀብት ከሁሉም በላይ መሬት ነው፤ ቀጥሎ ውሃ ነው፤ ቀጥሎ ጉልበት ነው፡፡ እነዚህ ናቸው የሀብት መሰረታችን፡፡ ስለዚህ የአማራ ክልል አመራር መሬቱን ይዞ፣ ህዝቡን  ይዞ፣ ውሃውን ተጠቅሞ  ማልማት ከቻለ ማደግ የማይችልበት ምክንያት የለም፡፡  ከፌዴራል ተመድቦ የሚሰጠው በጀት አይደለም ዋናው የልማት ምንጩ፡፡ ቅድም ያልናት መሬቱ፣ ውሃውና ጉልበቱ ናቸው፡፡ ይሄም ሆኖ እያለ በፌደራል ደረጃ ለክልሎች የሚመደብ በጀት በቀመር ነው፡፡ ዋናው የቀመሩ መሰረት ደግሞ የህዝብ ብዛት ነው፡፡  በፌደራል የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ካየንም በስርዓቱና በስርዓቱ መሰረት ነው፡፡ ይህ ሆኖ እያለ የፕሮጀክቶች ኣፈፃፀም ጉድለቶች ካሉ ተፈትሾ መስተካከል ኣለባቸው ተብለው ተቀምጠዋል፡፡

 ወደ ዋናው ጉዳይ ስመለስ እውነትም ለትግራይ ያደላ የመሰረተ ልማት ግንባታ ካለ፣ እውነትም ለትግራይ ያደላ የበጀት ምደባ ስርዓት ካለ "ይፈተሽ" ተብለዋል ይሄም ይታይ፡፡ "ይህ ተፈትሾ የሚስተካከል ነገር ካለ ይስተካከል" ተብሎ  በግልፅ መተማመን የተደረሰበት ነው፡፡ ስለዚህ የብአዴን ኣመራር ወደ ጎን ኣንጋጥጦ የሚያይበት ምክንያት የለዉም አሁን፡፡ የራሱን ውስጣዊ ችግር የሚፈታበት፣ ውስጠ ድርጅታዊ ዴሞክራሲው ምንድንነው የሚመስለው የራሱ የብአዴን? ከእህት ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት ምንድነው የሚመስለው? ብአዴን ራሱን እንዴት ነው የሚያየው? ከህወሓት ጋር፣ ከኦሆዴድ ጋር፣ ከዴኢህዴን ጋር ያለው ግንኙነት እንዴት ነው ራሱን የሚመዝነው? የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሰራቸው ስራዎች ምንድን ናቸው? ምንድን ነው ጉድለቱ? ያን የመሰለ ጉልበት ይዞ፣ ያን የመሰለ መሬት ይዞ፣ ያን የመሰለ ውሃ ይዞ ህዝቡን ከድህነት ለምንድን ነው ያላወጣው? ምንድን ነው የአመራሩ ችግር?  ወደ ውስጡ ማየት አለበት፡፡ ስለዚህ ወደ ውስጡ አይቶ ራሱን ከፈተሸ እውነትም "እኔ የአመራር ድክመት አለብኝ፣ ህዝብን በዚህ ደረጃ ጎድቼዋለሁ የሚል መደምደምያ ላይ ነው የሚደርሰው፡፡ እዛ ድምዳሜ ላይ ሲደርስ ነው ህዝቡ ተጠቃሚ የሚያደርገው፡፡

"የህወሓት 'የበላይነት አለ" ብሎ የሚያምን ከሆነ ደግሞ የህወሓት የበላይነት እንዲኖር ለምን እስካሁን ፈቀደ? ለምን ኣልታገለም እሱ? ለምን አድርባይ ሆኖ ቀጠለ? ያለን ስርዓትና ፌደራል ስርዓት ነው፤ የእኩልነት ስርዓት ነው፡፡ የእኩልነት ስርዓት ሆኖ እያለ ህወሓት የበላይ መሆኑን እየተመለከተ ለምን ዝም አለ? ለምን አልታገለም በወቅቱ? ስለዚህ እነዚህ ነገሮች በሙሉ የሚፈትሽበት ነው፡፡ ለመፈተሽ የሚያስችለው ደግሞ ምቹ ሁኔታ አለ፡፡ አንደኛ ቢያንስ የኢህኣዴግ ስራ ኣስፈፃሚ የሆኑ አመራሮች በዚህ ላይ  ተማምነው ወጥቷል፡፡ ቀጥሎ ያለው ማእከላይ ኮሚቴው ነው፤ ማእከላይ ኮሚቴውም ትግል ጀምሯል በውስጡ፡፡ በእንደዚህ መልኩ በየደረጃው ወደ ከፍተኛ ኣመራሩ፣ ወደ ታችም ስለሚወርድ እየተስተካከለ ይሄዳል፡፡ ልክ ህወሓት እንዳደረገው ሁሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ብአዴን ይለወጣል የሚል ጠንካራ እምነት ነው ያለኝ፡፡

ወይን፣ ስርዓቱን ማፍረስ የሚፈልጉ አካላት ህዝቡን በማቃቃር ዙሪያ ተጠምደው እየሰሩ ናቸው፡፡ ይህን ተግባራቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይም "ፍሬ እያፈራ ነው" ማለት የምንችልበት አጋጣሚዎች እያየን ነው፡፡ ብሔራዊ ድርጅቶቹ በመጠኑም ቢሆን የዚሁ ታክቲክ ሰለባ ሲሆኑ ያየንባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ የዚሁ መንስኤ ምንድነው?  ሊፈጥረው የሚችለው አደጋስ?

ጓድ ከበደ፣ ዘሮ ዘሮ ፀረ ሰላም ሀይሎች መንጠልጠያ አግኝተው ድል የሚቀናቸው  በኛ ድክመት ላይ ተንተርሰው ነው፡፡ እኛ ድክመቶቻችን ባስወገድን ቁጥር ፀረ ሰላም ሀይሎች የሚንጠለጠሉበት መሰረት እያጡ ይሄዳሉ፡፡ የኛ ድክመት ናቸው ለጠላቶቻችን የበለጠ ጉልበት እንዲያገኙ እያደረጓቸው ያሉት፡፡  ለምንድ ነው የኛ ድክመት መንጠልጠያ የሚሆኗቸው? ለምሳሌ እንውሰድ፤ ጠላት ለራሱ ፕሮፖጋንዳ ሲል የአንድ ብሄር የበላይነት አለ ብሎ ይሰብካል፡፡  የአንድ ብሄር 'የበላይነት' ብሎ ሲሰብክ የኛ ድርጅቶች በክልላቸው በደንብ መምራት ባለመቻላቸው ሁኔታው ሊንጠለጠሉበት ይፈልጋሉ፡፡ "እውነት ነው ትግራይ በተለየ ሁኔታ ለምታለች፤ የህወሓትና የትግራይ 'የበላይነት' አለ" ብሎ ያምናል፡፡ "እውነት ነው፤ ትግራይ በተለየ መንገድ ለምታለች" ብሎ ሰው መቁጠር ይጀምራል፡፡ "በመከላከያ ሳሞራ ነው ያለው" ይላል "በድህንነት 'እከሌ' ነው ያለው" ይላል፤ የሆነ ቦታ ላይ "እከሌ ነው ያለው" ብሎ ይቆጥራል፡፡ ያ ግለ ሰው ግን ለትግራይ አይደለም እየሰራ ያለው፡፡ የሚሰራው ለኢትዮጰያ ህዝቦች ነው፡፡ ግን ይቆጥርና  ለትግራይ ብቻ እንደሚሰራ አስመስሎ ያቀርባል፡፡ ይሄ ከጠላት ጋር ተሰማምተህ የጎራ መደበላለቅ ሲያጋጥም የሚፈጠር ችግር ነው፡፡

 የአማራ ክልል ላለፉት ሃያ ሰላሳ ዓመታት ከአማራ ክልል  ተወላጅ ውጭ ማንም ኣላስተዳደረውም፡፡ በፌደራል ስርዓቱ መሰረት ሲተዳደር ኖረአል፡፡ በጀት ቢሆንም በፌደራሉ ቀመር መሰረት ነው የሚከፋፈለው፡፡ ለየትኛውም ክልል በዚህች ፌደራል ሃገር እኩል ሜዳ ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ እኩል መወዳደርያ ሜዳ ላይ ተወዳድሮ ሀብት ማፍራትና ማደግ የራስ ጥረት ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡ ተወዳድረህ ለማሸነፍ ደግሞ የራስ ጥረት ስለሚጠይቅ አመራሩ የራሱን ድክመት ለመሸፈን ህወሓት ላይ፣ የትግራይ ህዝብ ላይ መንጠልጠያ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ አመራሩ ወደ ውስጡ ማየት ሲጀምር ህወሓት ላይ፣ የትግራይ ህዝብ ላይ መንጠለጠል ይቀራል፡፡ ይሄ ችግር የተፈጠረው እኛ  አመራሮቹ ስትራተጂካዊ ኣመራር መስጠት ባለመቻላችን የተፈጠረ ነው ብሎ ማመን ሲጀምር ሰበብ ኣስባቡ ይቀራል፡፡ ስለዚህ ያኔ ጣት መቀሰሩ ያቆማል፡፡

በነገራችን ላይ እኔ ይሄን የተዛባና የዘቀጠ አስተሳሰብ መስማት የጀመርኩት አሁን ኣይደለም፤ ገና በ1984 ዓ/ም ጀምሮ ነው፡፡ 1983 ዓ/ም ደርግ ተወግዶ 1984 ዓ/ም ካድሬዎቻችን በምናወያይበት ጊዜ ትግራይ ሶስት ሴንቲ ሜትር ወደ ታች ዝቅ ብላለች አሉን፡፡ ለምን? ስንል፣ ከመሀል አገር ተጉዞ ተጉዞ የሄደው ሀብት መሸከም ስለአቃታት ዝቅ ብላለች ብሎ የሚያነሳ ካድሬ ነበረ፡፡ ይሄ ጠላት የሚፈብርከው ነው፡፡ የውሸት ፋብሪካ ውስጥ የተፈበረከ ውሽት ሳያላምጥ የሚውጥ አስተሳሰብ ስላለ ነው፡፡ ያ እንዳልሆነ ሲገነዘብ ግን የትግራይ ህዝብ ዛሬም አንጀቱን አስሮ ተራራውን በጥፍሩ እየቆፈረ የሚኖር፣ ከ27 በመቶ በላይ ህዝቡ ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ህዝብ መሆኑ ይረዳል፡፡ የሀገር አቀፍ የድህነት መጠኑ 23 ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ግን ከዚሁ በከፋ መልኩ 27 በመቶ ነው ከድህነት ወለል በታች እየኖረ ያለው፡፡ ይሄ እኛ የሰራነው አይደለም፡፡ ሀገራዊ ስታስቲክ ኤጀንሲ በራሱ ሞያተኞች ያረጋገጠው ሀቅ ነው፡፡ እንዲህ መሆኑ የሚያስደስት አይደለም፡፡

የከፋ የሚያደርገው ግን በድህነት ውስጥ እየኖረ የትግራይ ህዝብ የተለየ ጥቅም አግኝቷል ብሎ መናገር ለፖለቲካ ፍጆታ ወይም ለሌላ (ምናልባትም ትግራይን ለማጥላላት ለሚፈልግ ሀይል) ካልሆነ በስተቀር ምንም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ እውነታው ይሄ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ነገ ህዝቦቹ ከመጠራጠር እየወጡ የጋራ ኮንፈረንሶች፣ የህዝብ ለህዝብ መድረኮች እየተፈጠሩ ሲሄዱ የትግራይ ህዝብ ሲጎበኝ ያኔ ሀቁ ይጠራል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ኣኳያ ብአዴን ቆም ብሎ የራሱን ውስጣዊ ድክመት መፈተሽ አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ህወሓትና ብአዴን ለአንድ ዓላማ በአንድ ምሽግ እየወደቁ የመጡ ድርጅቶች መሆናቸውን ተገንዝቦ አሁንም  ከመጠራጠር ወጥቶ ህወሓት ስትራተጄክ የትግል ወዳጁ መሆኑ አምኖ በጋራ ትግሉን መግፋት አለበት እላለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የትግራይና የአማራ ህዝብ አንድ ህዝብ መሆኑ፣ ወንድም ህዝብ መሆኑ፣ ምናልባትም እጣ ፈንታው አንድ መሆኑ አምኖ መታገል አለበት፡፡

ወይን፣ ከዚሁ ጋር ተያይዘው በተለይ በአንድንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች "የአማራን ህዝብ በትግራይ ተወላጆች ላይ እንደተነሳ" ለማስመሰል የሚሰሩ ሴራዎች እያየን ነው፡፡ ይህንን እንዴት ነው መፍታት የሚቻለው፡፡ 

ጓድ ከበደ፣ ለኔ ይሄ  ጊዚያዊ ችግር ነው፡፡ ዘሮ ዘሮ ለጊዜየው የትግራይ ተወላጆች በዚሁ ሁኔታ ሰለባ ሆነዋል፤  ንብረታቸው የተቃጠለባቸው አሉ፤ ልክ እንደ ሌላ አገር ዜጋ ከቤታቸው ላይ "ውጡ" ተብለው የመባረር አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ ይሄ መሆን አልነበረበትም፡፡ በእኔ እምነት ይህን ያደረገው የአማራ ህዝብ ነው የሚል እምነት የለኝም፤ ልያደርገው ኣይችልም፡፡ ይህን ሲደረግ ጎንደርም ላይ ህዝቡ ወንድሞቹን ደብቆ፣ ተከላክሎ ለማዳን ሞክረዋል እኮ፡፡ አሁንም ወልድያ ላይ ተመሳሳይ ነገር ሲደረግ ህዝቡ እየተከላከለ ተግባሩ ለማውገዝ ጥረት አድርጓል፡፡ ግን ፀረ ሰላም ሀይሎች በህዝቡ ውስጥ ገብተው ሆን ብለው፣ "የአንድ ብሄር የበላይነት አለ" ብለው እየሰበኩ የትግራይ ተወላጆችን በማጥቃት ድል እናገኛለን ብለው ስልት ቀይሰው ተንቀሳቅሷል፡፡ ይሄ የሆነበት ምክንያት ህዝቡ ሰላልነቃ ነው፡፡ ህዝቡ ሲነቃ ይህን አይነት ሁኔታ በፍፁም ተቀባይነት ኣይኖረውም፡፡ እነዚህ ፀረ ሰላም ሀይሎች ማንም ሰሚ ኣያገኙም፡፡ እውነቱን በሚገነዘቡበት ጊዜ ዘሮው ጠላቶቻቸው እንደሚዋጉ መታወቅ ኣለበት፡፡ ለዚህ ተግባር የብአዴን ታጋዮችና የአማራ ህዝብ እያወገዘው ነው፡፡ ተግባሩ ከመዋቅራችን የተወሰኑ የተበላሸ ኣስተሳሰብ ያላቸው ግለሰዎች እና የጠላት ሀይሎች በቅንጅት የሚፈፅሙዋቸው ደባዎች ናቸው፡፡ እነዚህን መታገል ያስፈልገናል፡፡ አሁንም እየታገልን ነው፡፡ ቆቦ ላይ፣ ወልድያ ላይ ለተፈጠረው ሁኔታ ለታገሉ ታጋዮቻችን ቤታቸውን ተቃጥሏል፡፡ በድፍረት፣ በፍፁም ህዝባዊነት "ይቃጠል" ብለው ደረታቸው ነፍተው ነው የታገሉት፡፡  ስለዚህ ማየት ያለብን የነዚህ ፀረ ሰላም ሀይሎች ፍላጎት የትግራይ ህዝብ ብቻም ኣይደለም፡፡ እነዚህ ሀይሎች ስርዓቱን፣ አገሪቱን ነው ማፍረስ የፈለጉት፡፡ ይሄ ሁኔታ ለአማራ ህዝብም ለብአዴን አመራርም የሚተርፍ መሆኑ በተግባር እየታየ ነው፡፡ ይህንን ተግባር የአማራም የኢትዮጵያም ህዝብም በጋራ ማውገዝ ኣለባቸው እላለሁ፡፡

ወይን፣ ኢህአዴግ ግምገማውን እንዳጠናቀቀ ባወጣው መግለጫ እያንዳዱ ብሄራዊ ድርጅት ራሱን የሚፈትሽበት መድረክ እንደሚቀጥል ኢፋ አድርጓል፡፡ ከዚሁ ምንድነው የሚጠበቀው?

ጓድ ከበደ፣ ከእያንዳዱ ድርጅት የሚጠበቀው በእኔ እምነት የጥገኛ ዝቅጠት አደጋዎች በሚገባ ታግለው ይወጣሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ከሙስና፣ ከብልሹ አሰራር ከጠባብነት፣ ከትምክህት ጋር የተያያዙ አስተሳሰቦችን ታግለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመሩን የሚያጠናክሩ አቅሞችን ይዘው ይወጣሉ ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሁሉም ድርጅቶች ይሄን ማድረግ  ከቻሉ ኢህአዴግ እውነቱም የተሀድሶ ሀይል ሆኗል ማለት ነው፡፡ ህዝቡ ጋር ያሉትን ችግሮችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፈታት የሚያስችል አቅም ይኖረዋል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ስለዚህ ከብሄርዊ ድርጅተቹ የሚጠበቀው አሁንም ቢሆን መድሃኒታችን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችን ነው፤ ጥገኛ ሀይል መቼውም ቢሆን ሀይል ሊሆነን አይችልም፡፡ ለጊዜው ከኛ ጋር ሆኖ አይዞን ሊለን ይችላል፤ ከኛ ጋር ሊሰለፍ ይችላል፡፡ የማታ ማታ ግን የሚክድ ሀይል ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመርና አቅም ላይ በጥንካሬ ቆመው ይሄን ይዘው ወደ ፊት እየታገሉ ሌሎችም ወደዛ እንዲሰባሰቡ በማድረግ ፀረ ጥገኝነት ትግላችን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ ብሄራዊ ድርጅቶቹ አሁን ከምያካሂዱት መድረክ የሚጠበቅባቸው ኪራይ ሰብሳቢ ኣመራሮችን፣ ኔትዎርክ የሰሩትን፣ በሌላው ህዝብ ላይ ጥላቻ ያላቸውን መሪዎችን በሚገባ ታግሎ ቦታቸውን ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል ብየ አስባለሁ፡፡ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ኣመራሮች ተጠያቂ ማድረግ አለበት፡፡ ህዝቦቹ ከግጭት፣ ከመፈናቀል፣ ከሞት አደጋ ተርፈው በፍቅርና በእድገት የሚኖሩበትን ሀገር ለመፍጠር ቆርጦ መነሳት አለበት፡፡ ይሄ ማድረግ ከቻልን እውነትም ኢህአዴግ ታድሶ አገሪትዋ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አገሮችን ተርታ ለማሳለፍ የያዘውን ዕቅድ ተፈፃሚ ይሆናል ብየ አምናለሁ፡፡

ወይን፣ በአጠቃላይ ኢህአዴግ ከችግሮቹ ወጥቶ ወደ ተለመደው ባህሪው ለመመለስ ያለው ጥሩ ዕድልና ፈተናዎቹ እንዴት መገምገም ይቻላል?

ጓድ ከበደ፣ ከሁሉም  በላይ እኔ ጥሩ ዕድል አድርጌ ያየሁት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ለ17 ቀናት በግምገማ ሲቀመጥ ተመሳሳይ ኣቋም ይዞ መውጣቱን ነው፡፡ ምክንያቱ ስጋቶች ነበሩን፡፡ ይሄ ሀይል ተከፋፍሎ ይወጣ ይሆን? አንድ አይነት ኣቋም ይዞ ይወጣ ይሆን? የሚል ሁላችንም ጥርጣሬዎች ይዘን ነው የገባነው፡፡ ግን ብሩህ ተስፋ ይዘን ወጣን፡፡ አንድነት ይዘን፣ ተማምነን ነው የወጣነው፡፡ ይሄ ለኢህአዴግ ጥሩ ዕድል ነው፡፡

በስጋት ደረጃ የሚቀመጠው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አሁንም ቁጥሩ ትንሽ ነው፡፡ ወደ ታች ስንሄድ የማዕከላይ ኮሚቴው ቁጥር ብዙ ነው ፡፡ ስለዚህ በየድርጅቱ በማዕከላይ ኮሚቴ ደረጃ በሚደረገው ስብሰባ የተፈለገው አቋም ይዞ የመውጣትና ያለመውጣት ጉዳይ አሁንም ጠንካራ ትግል የሚጠይቅ ነው፡፡ የኢህአዴግ ስራ ኣስፈፃሚ ኮሚቴ ተመሳሳይ ኣቋም ይዞ ቢወጣም ማዕከላይ ኮሚቴው ካልደገፈው አደጋ ሊኖረው ይችላል፡፡ አመራሩ ሲከፋፈል ሌላ የፖለቲካ ልዩነት ያለው ይመስል ተከፋፍሎ ሌላ ብጥብጥ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ስጋቶችን ማስወገድ የሚያስችል ትግል ማካሄድ ይጠይቃል፡፡ "እከሌ ጥግተኛ ነህ ውጣ፣ እከሌ ትምክህተኛ ነህ ውጣ፣ እከሌ እነደዚህ ነህ ውጣ" የሚለው ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ይሄ ግድ ነው፡፡ ይሄ ሲደረግ ሰዎች የመማር ዕድል እንድያገኙ፣ በፀፀት መልክ እንድያዩት፣ ተፀፅተው ደግሞ ህዝባቸውና አገራቸው ለመካስ የሚጥሩበት፣ እልህና ወኔ እንዲሰንቁ የሚያደርግ ኣቅጣጫን  የተከተለ ግምገማም መካሄድ አለበት፡፡ ይሄ ማለት ግን በትምክህት ላይ፣ በአድርባይነት ላይ በሙሰኞች ላይ መደራደር አለብን ማለት ደግሞ ኣይደለም፡፡

ጥፋተኛ ጥፋተኛ  ነው፡፡ በህግ የሚጠየቅም ሊሆን ይችላል፡፡ ግን በተጨባጭ ግምገማ መመራት አለበት፡፡ በዚሁ ጊዜ ንፁህ ሆኖ ለሚታገል ሰውም ኔትዎርክ ፈጥረው የሚረባረቡበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ትግል ንፁህ ሰዎችንም እንዳናጣ፣ ሌቦችን ደግሞ አቅፈን እንዳንሄድ የሚያደርግ ትግል መካሄድ አለበት፡፡ ይህን ትግል ስናካሂድ ፈተናዎች እየተቀረፉ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ለእኔ ተስፋውም አለ፤ ስጋቱም አለ፡፡ የሚያይለው ግን ለእኔ ተስፋውን ነው፡፡ ምክንያቱም ህዝባችን "ኢህአዴግ ችግሮቹን አስተካክሎ ሊመጣ የሚችል ድርጅት ነው ብሎ ስለሚያምን በተስፋ እየጠበቀ ነው፡፡ ስለሆነም ህዝቡ ከጎናችን ነው ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ መላው ኣባሎቻችንም ቢሆኑ ከሚሰጣቸው አቅጣጫ የሚወጡ አይደሉም፡፡ ድርጅታቸውን ያላቸው የሚሠሙ ናቸው፡፡ ሶስተኛ  ወጣቱም ቢሆን የተወሰነ ሀይል ነው እንጂ በየአካባቢው ረብሻ የሚያስነሳው አብዘሀኛው ወጣት ወደ ረብሻ የሚገባ አይደለም፡፡ በተለያዩ ስራዎች ታቅፎ ህይወቱ ለመለወጥ በተስፋ የሚኖር ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ተስፋዎች ይበልጥ  እጅ ለእጅ ተያይዘን ለለውጥ እንድንተጋ የሚያደርጉ በመሆናቸው ለእኔ ትልቅ አቅም ናቸው፡፡ ስለዚህ የሚያመዝነው ጨለማነቱ ሳይሆን ተስፋውን ነው፡፡ ስትራተጂክ አመራሩ ተበትኖ ቢሆን ኖሮ፣ ተከፋፍሎ ቢሆን ኖሮ ይሄ እድል አይመጣም፡፡ ግን ሁሉም የኢህአዴግ ኣመራር (ኮር ኣመራሩ) አንድ አይነት ኣቋም ይዞ ስለወጣ ይህን ሌላ ተፅዕኖ እየፈጠረ የመለወጥ ተስፋው በእጅጉ የሰፋ ነው ብየ ነው የማምነው፡፡

ወይን፣ መልእክት ካልዎት

ጓድ ከበደ፣ በመጀመርያ እንኳን ለየካቲት 11  43ኛው ዓመት የትግራይ ህዝብ የትግል ልደት በዓል አደረሰን እላለሁ፡፡ የትግራይ ህዝብ፣ የህወሓት ታጋዮች በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረትና ኢትዮጵያ አገራችን ከድህነት ወጥታ ወደ በለፀገ ደረጃ እንድትሸጋገር የከፈሉት መስዋእትነት ትልቅ ነው፡፡ ይሄ መስዋእትነታቸው በከንቱ እንዳይቀር ሁላችንም ከጎናቸው መሰለፍ አለብን፡፡ ሌላው ህዝብም ቢሆን የትግራይ ህዝብ ትግል ማክበር አለበት፡፡ እያንዳንዱ ቤተሰብ በትግሉ ጊዜ ከአንድና ሁለት ልጆቹ በላይ ከፍሏል፡፡ ልጆቹን ለመስዋእትነት ያቀረበ ነው የትግራይ ህዝብና ህወሓት፡፡ ልጆቹን ገብረዋል፤ ንብረቱን ወድሟል፡፡ በርካታ መስዋእትነት ከፍሏል፡፡ አይናቸው የጠፉ፣ እጃቸው እግራቸው የተቆረጡ ታጋዮች አሉበት፡፡ ይህን ለመሰለ ዋጋ ለከፈሉ ታጋዮች እንኳን "ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል" ብሎ የጠየቀ ድርጅት አይደለም ህወሓትና የትግራይ ህዝብ፡፡ "የኢትዮጵያ ህዝብ ሲጠቀም እንጠቀማለን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በእኩልነት ሲኖር እኛም በእኩልነት እንኖራለን" ብሎ የሚያስብ ድርጅትና ህዝብ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ የትግራይ ህዝብ ከሌላው ህዝብ የተለየ የበለጠ ልዩ ጥቅም የማይፈልግና ያላገኘ መሆኑ በዚሁ አጋጣሚ እንዲገነዘብ እፈልጋለሁ፡፡ የትግራይ ህዝብና ህወሓትም በስሙ የሚነግዱትን ጥቂት ጥገኛ ሀይሎችን በብቃት መታገል አለባቸው፡፡ የትግራይን ድርጅት ህወሓትን ጥላ ሸት የሚቀቡ፣ የትግራይ ህዝብን ሳይጠቀም እንደተጠቀመ የሚያስመስሉ ጥገኛ ሀይሎች አሉ፡፡ እነዚህን ጥገኛ ሀይሎች በጋራ መታገል አለብን፡፡ በመጨረሻ ትግሉ የጋራ ነው፤ ተሳስረን በአንድነት እስከመጨረሻ እንዘልቃለን፡፡ ለህወሓት መልካም የልደት በዓል፣ ለትግራይ ህዝብም የጀመርከውን ትግል፣ ከድህነት የመውጣት ትግልም ይሁን ህወሓትን የማስተካከል ትግል ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እላለሁ፡፡

ወይን፣  በወይን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ስም አመስግናለሁ

ጓድ ከበደ፣  እኔም ኣመሰግናለሁ፡፡


alena ember where do we

መፅሄት ክልሰ ሓሳብ ህወሓት 3

ኣውርድ መፅሄት ክልሰ ሓሳብ ህወሓት 3

መፅሄት ክልሰ ሓሳብ ህወሓት 2

ኣውርድ መፅሄት ክልሰ ሓሳብ ህወሓት 2

መፅሄት ክልሰ ሓሳብ ህወሓት 1

ኣውርድ መፅሄት ክልሰ ሓሳብ ህወሓት 1

ወይን ብፒዲኤፍ

ኣውርድ ጋዜጣ 971
ፍሉይ ሕታም መፂሄት
አውርድ መፅሄት ለካቲት 2010